
*===================*
በዶ/ር መስፍን ሙሉጌታ የተጻፈ #ፍትሃዊ_ሪፐብሊክ_የተሰኘ መጽሐፍ በወልቂጤ ከተማ ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።
መጽሃፉ በወልቂጤ ከተማ መመረቁ በአካባቢው አዳዲስ ደራሲያንና አንባቢያን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገለጸ፡፡
የመጽሐፉ ዝግጅት ያተኮረው ስለ ሰላም፣ ስለ ሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ዜግነት ክብር፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ አካታችነት፣ ስለ መልካም አስተዳደር እንዲሁም በመንግስትና በህዝብ መካከል ሊኖር ስለ ሚገባው ጤናማ ግንኙነት በአዲስ እይታ ይዞ ብቅ ያለ መጽሐፍ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለጹ።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ-ጹሑፍ መ/ር ካሚል ኑረዲን በመጽሐፉ ምረቃ ወቅት እንዳሉት ፍትሃዊ ሪፐብሊክ እውነትና ፍትህ ምን እንደሆነና የአለምን ጉድለት በደንብ የሚያሳይ ከወገንተኝነት ነፃ በሆነ መልኩ የተዘጋጀ ነው።
ደ/ር መስፍን ሙሉጌታ በመንግስትና በተለያዩ የግል ድርጅቶች በባለሙያነትና በአመራርነት በማገልገል በርካታ ልምድ ያካበቱ ናቸው። እነዚህም በቀድም የጉራጌ ልማት ማህበር በህዝብ ግንኙነት፣ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት እንዲሁም ደቡብ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት በሲኒየር ኢኮኖሚስትነት አገልግለዋል።
ከሀገር ውጪ በጀርመን በዴካ ባንክ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያነት፣ በጀርመን ባንክ የአፍሪካ ግብርናና ኢንቨስትመንት አማካሪነት ያገለገሉ ሲሆን በሰሜን አሜሪካ፣ በጀርመን፣ በኔዘርላንድ፣ በፓርቹጋል፣ በጣሊያን፣ በቱርክ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያና በታይላንድ ዩኒቨርስቲዎች የተለያዩ የምርምር ስራዎቻቸውን በማቅረብ የሚታወቁ አለም አቀፍ ምሁር መሆናቸው ከዶ/ር መስፍን ሙሉጌታ ግለ ታሪክ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የመጽሐፉ በወልቂጤ ከተማ መመረቅ በአካባቢው አዳዲስ ደራሲያንና ተጨማሪ አንባቢያን እንዲፈጠሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በምረቃው ወቅት ተገልጿል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።







