






ህዳር 04/2017 ዓ.ም
የወልቂጤ ከተማ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች የድርሻቸው እንዲወጡ ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሀይማኖት አባቶች ጋር የውይይት አካሂዷል።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በመግበያ ንግግራቸው ወቅት እንዳሉት የወልቂጤ ከተማ ብዙ ታሪክና ረጅም እድሜ ያላት ቢሆንም ከሌሎች አቻ ከተሞች አንፃር ግን በቂ እድገት አላስመዘገበችም::
የጉራጌ ማህበረሰብ ሰርቶ የመለወጥ ተምሳሌት ማህበረሰብ እንደመሆኑ መጠን ከተማዋም ማህበረሰቡ የሚመጥን መሆን እንዳለበትና በገጠር በህብረተሰቡ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በከተማውም ማህበረሰብ ሊደግም እንደሚገባ ያስፈልጋል።
ከተማው እንዳትለማ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ህገ ወጥ የመንደር የሀይማኖት፣የብሄር እና የዘረኝነት አደረጃጀቶች በማስቀረት ብልሹ አሰራርን አጥብቀን እንታገላለን ብለዋል።
የከተማው ፕላን ተግባራዊ ለማድረግና የድንበር ጣልቃ ገብነትን ለማስቆም ከሚመለከተው አካል ምላሽ እየተጠበቀ በመሆኑ ህዝቡ በትግስት መጠበቅ አለበት ያሉ አቶ ሙራድ ከዚህ በተያያዘ በህብረተሰቡ ላይ ሁከት የሚፈጥሩ ሀሳቦችና አመለካከቶች ማረም እንደሚገባ አስገንዘበዋል።
ከተማዋ ለማልማት የከተማው ገቢ አሰባሰብ ሊሻሻል ሲገባው በርካታ የንግድ ተቋማት ግን ገቢን በአግቡ እየከፈሉ ባለመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ እና ተጠቃሚው ደረሰኝ በመስጠት እና በመቀበል ሂደቱ የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
መሪና ተመሪው ከተቀናጀ ማንኛውም ልማት ማሳካት ይቻላል ያሉት አቶ ሙራድ ይህንን የአሰራር ስርአት በመዘርጋት የከተማው እድገትና ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የሚቀረፍ ሲሆን የወልቂጤ ከተማ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች የድርሻቸው እንዲወጡ አቶ ሙራድ አሳስበዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ታደለ በቀለ በከተማው የተጀማመሩ የልማት ስራዎች እንዲጠናቀቁ የገቢ አቅምን ማሳደግ ፣ህዝቡና መንግስት መቀናጀት እና ህግን ማስከበር የግድ ይላል።
በከተማው በተመረጡ ቦታዎች የኮሊደር ልማቱ የማስጀመር ስራ እንደሚከናወን ያመላከቱት ዋና ተጠሪው መሰል አይነት ከተማው የማስዋብና ጽዱ ከተማ ለመመስረት ህብረተሰቡ ከፍተኛ ድርሻ አለው ሲሉ ገልጸዋል።
ለአብነትም ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ እረገድ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት ብለዋል አቶ ታደለ።
ወልቂጤ ሰላምዋ የተረጋገጠ ለኑሮ አመቺ ከተማ ለማድረግ ህብረተሰቡን አካባቢውን በነቂስ መጠበቅ እንዳለበት የመከሩ ሲሆን ህገ ወጥ እና ዘራፊ ሀይሎች በመበራከታቸው ለህግ አሳልፎ መስጠት ያስፈልጋል።
በየጊዜው በከተማው የሚስተዋለው የአመራር መለዋወጥ ችግር ለመቅረፍ በቅርቡ ጠንካራና ወቅቱን የሚመጠን አመራር ለመሾም ጥረት መደረጉ አመላክተዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች በበኩላቸው ቅድሚያ አመራሩ የህዝቡ አንገብጋቢ ችግር ምን እንደሆነ መለየት ይጠበቅበታል።
በከተማው የተጀማመሩ የልማት ስራዎች በወቅቱ አለመጠናቀቅ ፣ በየጊዜው የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ፣ የነበሩን መልካም እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ መሆናቸው እና በየጊዜው የአመራር መቀያየር ለከተማው እድገት መስተጓጎል መፍጠሩ ለአብነት አንስቷል።
ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ እየጠየቀ ያለው የከተማው ማስተር ፕላን በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲደረግና የድንበር ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ጠይቀዋል።
አክለውም የውሃ እጥረት ችግር በዘላቂነት አለመፈታቱ፣ የተጀማመሩ የመሰረተ የልማት ስራዎች በወቅቱ አለመጠናቀቃቸው፣ወጣቶች ብድርን በወቅቱ አለመመለስ፣ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ዝርፊያ መኖሩ፣የታቀዱ እቅዶች አፈጻጸማቸው ሙሉ ለሙሉ አለማሳካት እንዳለ አንስተዋል።
ህብረተሰቡ አካባቢውን ከቆሻሻ ጽዱ ማድረግ ፣መንገድ የሚዘጋው በማስታገስ፣አካባቢውን በመጠበቅ እና የሚጠበቅበትን ግብር በመክፈል የድርሻው ሊወጣ ይገባል ያሉ ሲሆን የሀይማኖት አባቶች ትውልዱን በስነ ምግባር ማነጽ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ህዝብና መንግሥት አንድ ከሆነ እና ከተደማመጠ የከተማው እድገትና ሰላም በአፋጣኝ ማረጋገጥ ስለሚቻል በዚህም የበኩላቸው እንደሚወጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች አስታውቀዋል።






