በ2015 በጀት ዓም በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ በተጨባጭ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ ።
እንደ ወረዳው የህብረተሰቡ የመልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በተከናወኑ ስራዎች አበረታች የሆኑ ተግባራቶች መከናወናቸውንም ተጠቁሟል ።
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በ2015 በጀት ዓም በዋናነት የተለያ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ዙሪያዩ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ በተለይም በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች በተቻለ አቅም ህብረተሰቡን ተጠቃ ለማድረግ በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆኑንም አመላክተዋል ።
በጤና ዘርፍ 3501 እናቶች በሰለጠነ ባለሙያ በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት ያገኙ ሲሆን 3358 ጨቅላ ህፃናት ሁሉንም አይነት ክትባት እንዲያገኙ አገልግሎት ተሰጥቷል ብለዋል ።
በዚሁ ዘርፍ ከፍተኛ አፈፃፀም ያላቸው ሞዴል ተቋማት ከመፍጠር አንፃር 75% ማድረስ ተችሏል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ምቹ የጤና አካባቢ ለመፍጠር በተደረገው ጥረትም ከ1ሚሊየን ብር በላይ የጤና ባለሙያ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፡ ቆሻ ማቃጠያ ግንባታ እና ሌሎችም ተያያዥነት ያላቸው ስራዎች ተከናውኗል ።
በትምህርት ዘርፍም በተማሪዎች ውጤት ላይ የነበረው ስብራት ለማካካስ በርካታ የንቅናቄ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን የትምህርት ቁሳቁስና የተለያዩ የጥምርታ ስራዎች ፡ የመማሪያ ክፍል ጥገናና ግንባታ ስራዎች መሰራቱንም ጠቁመዋል ።
እንደ ወረዳው በበጀት ዓመቱ 32 የመማሪያ ክፍሎች ፡ 17 የቅድመ መደበኛ ግንባታ ስራዎች 32 የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለመስራት ተችሏል ያሉት አቶ ዘውዱ በወረዳው ለረጅም ግንባታቸውን የተጓተተና የህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥያቄ የነበሩት 3 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ የሚሆን 3.6 ሚሊየን ብር የወረዳው መንግስት በመመደብ የግንባታ ቁሳቁሶች መግዛቱንም አብራርተዋል።
ሌላው በኢኮኖሚ ዘርፍ በከተማና ገጠር በርካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን በከተማ ለተለያዩ አገልግሎቶች 5 ሄክታር መሬት ማቅረብ የተቻለ ሲሆን ለዚህም 4.6 ሚሊየን ካሳ ተከፍሏል ያሉት ዋና አስተዳዳሪ ከተሞች ሳቢና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ 1.3 ኪ.ሜ የመንገድ ስራና እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ የመትከል ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በመንገድ ልማት ዘርፍም rr10 ደረጃ 10.5 ኪ.ሜ እና rr30 ደረጃ 15.3 ኪ.ሜ የተገነባ ሲሆን በአጠቃላይ እንደ ወረዳው በመንገድ ልማት ስራ ከ33 ሚሊየን በላይ በመንግስትና በህብረተሰበ ትብብር መሰራቱንም አብራርተዋል።
በግብርናው ዘርፍም በምርት ዘመኑ 11ሺህ 240 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ማልማት ተችሏል ያሉት አቶ ዘውዱ ከዚህም 1 ሚሊየን 446 ሺህ 723 ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ብለዋል።
እንደ ወረዳው ውጤት ከመጣባቸውና ህብረተሰቡ ባለቤት ሆኖ ከሚያከናውናቸው ተግባሮች መካከል አንዱ የሆነው ተፋሰስ ልማት ስራ በበጀት ዓመቱ 7ሺህ 707 ሄክታር መሬት መልማቱን ጨምረው የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው በበልግ ልማት በተለይም በድንች 3ሺህ 90 ሄክታር ታርሶ በዘር ተሸፍኗል ብለዋል ።
በፍራፍሬ ልማት ዘርፍም 920 ሺህ የቡና ችግኝ እና 53 ሺህ የአቮካዶ ችግኞችን በማፍላት በአሁን ሰዓት ለአርሶአደሩ ለተከላ እየተሰራጩ ይገኛሉ ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በእንስሳት ማሻሻል ዘርፍም 1 ሺህ 261 ላሞችና ጊደሮች የማዳቀል ስራ መሰራቱንም አብራርተዋል ።
እንደ ወረዳው በስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ በገጠርና ከተማ 2249 ወጣቶች በስራአጥነት ተለይተው 1462 ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን ከነዚህም መካከል በተለይም በግብርናው ዘርፍ ለተደራጁ 20.7 ሄክታር መሬት ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩት የልማት ስራዎች እንዲሳኩ ቁልፍ ጉዳይ የሆነው የገቢ አሰባሰብ ስራ ላይ እንደ ወረዳው ውጤታማ የሆነ ስራ ተሰርቷል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በበጀት ዓመቱ ለማሰባሰብ ከታቀደው 84 ሚሊየን 246ሺህ 98ብር ውስጥ 90 ሚሊየን 108ሺህ 40ብር ወይንም የእቅዱ107% ገቢ ማሰባሰብ መቻሉንም አብራርተዋል።
እንደ ወረዳው በበጀት ዓመቱ በየተቋማት የታቀዱ ስራዎች በአግባቡ እንዲፈፀሙ በተሰሩ ስራዎች ህብረተሰቡን ተጨባጭ ያደረጉ ስራዎች ተከናውኗል ያሉት አዘውዱ በቀጣይም የህብረተሰቡ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የበለጠ ስራ ለመስራት ጥረት ይደረጋልም ብለዋል ።








