
=========================
ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ስርዓትን በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል የተቀናጀ ስራ እንደሚጠይቅ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት ገለፀ።
ፅ/ቤቱ በጎልማሶች ትምህርት አፈፃፀም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የእዣ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ እንደገለፁት ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህር በአግባቡ አጠናክሮ ማስቀጠል የተማረና በኢኮኖሚ የዳበረ ማህበረሰብ በሀገራችን ብሎም በወረዳ እንደሚፈጠር ትልቅ እገዛ እንዳለው በመገንዘብ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል ።
ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ስርዓትን በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል የተቀናጀ ስራ እንደሚጠይቅ የገለፁት አቶ ተጠምቀ በዘርፉ ያሉትን መሰረታዊ የሆኑ ክፍተቶች በመለየትና እንዲታረሙ በማድረግ እንደ ወረዳው ጎልማሶች በሁሉም ጣቢያ በሚባል ደረጃ እንዲማሩ አስፈላጊውን ርብርብ ሊደረግ ይገባል ብለዋል ።
የእዣ ወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት ም/ ሀላፊ አቶ አስቻለው ወልዴ በበኩላቸው ስልጠናው በተቀናጀው ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትን አፈፃፀም ወቅት የሚገጥሙ ችግሮችና በሚፈቱበት መንገድ ዙሪያ ላይ ያተኮረ በመሆኑም በቀጣይ በዘርፉ የተሻለ ስራ እንዲሰራ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የጎላ ነው ብለዋል።
የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ለመደበኛው ትምህርት የመማር ማስተማር ሂደት አጋዥ ነዉ ያሉት አቶ አስቻለው ጎልማሶች በቀለም ትምህርት ብቻ ሳይሆን በክህሎትና የአመለካከት ለዉጥ እንዲያመጡ በዘርፉ ያሉትን ማነቆዎች ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ በማድረግ መፍታት ይገባልም ብለዋል ።
በፅ/ቤቱ የጎልማሶች ትምህርት ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ ወ/ሮ ጤና ፈቃዱ በበኩላቸው በወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች በ69 ጣቢያዎች በሁለቱም ደረጃ 5926 ጎልማሶች ተመዝግበዋል ያሉት ወ/ሮ ጤናለም እነዚህም በአግባቡ ከመማር ጋር ክፍተት ያለበት በመሆኑ በቀጣይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ ይገባልም ብሎም ።
በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ዘርፉን በዘላቂነት ውጤታማ ለማድረግ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዘርፉን በበጀት ከመደገፍ አንስቶ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከረ ድጋፍ ሊያደረግ እንደሚገባም ወ/ሮ ጤና አሳስበዋል።
በእለቱም አንዳንድ ጣቢዎች በተሟላ መልኩ ከማስተማር አንፃር ክፍተቶች መኖራቸው ፡ አመቻቾች አለመሟላትና ሌሎችም ክፍተቶች ተነስተው በቀጣይ መፍትሄ በሚያገኙበት መንገድ ላይ በሰፊው ውይይት ተደርጎባቸዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው ።







