
ነሀሴ 16/2015 ዓ.ም
==============================
ውጤታማ ፡ ህጋዊና ተጠያቂነት ያማከል የመሬት አስተዳደር ስርዓት በመፍጠር መልካም አስተዳደር ማስፈን እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ መሬት አስተዳደር ፅ/ቤት ገለፀ ።
በወረዳው የመሬት አስተዳደር እና የመረጃ ስርዓትን ማዘመን ላይ ትኩረት ያደረገ በካልም ላንድ ፕሮጀክት ድጋፍ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል ።
በእለቱም የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ እንደገለፁት እንደ ወረዳው በገጠር መሬት ላይ የህግ ማዕቀፎች ተግባራዊ በማድረግ ጠንካራ የመሬት ስርዓት ለማስፈን የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አመላክተዋል ።
በተለይም የወል መሬት አጠቃቀም በተመለከተ በቀበሌ ላይ ያሉትን አንዳንድ ችግሮች በቶሎ እንዲቀረፉ የዚህ ባለድርሻ አካል ሚናው የጎላ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ለዚህም ጥራት ያለው መረጃ በአግባቡ በማደራጀትና አጣርቶ ለሚመለከተው አካል በመስጠት እንዲሁም በእርሻ መሬት ላይ የባህር ዛፍ ችግኝ እንዳይተከል በመቆጣጠርና በማስገንዘብ የተቀናጀ ጠንካራ ስራ መስራት ይጠይቃልም ብለዋል።
በቀጣይም በቀበሌ ደረጃ የተዋቀሩ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ኮሚቴዎች በአዋጁ መሰረት በየአካባቢያቸው አስፈላጊውን መረጃዎች ማደራጀት ይገባቸዋል ያሉት አቶ ዘውዱ በተለይም በወል መሬት አስተዳደርና ሌሎችም መሬቶች ባላስፈላጊ መልኩ ከመጠቀም ጋር እየተስተዋሉ ያሉትን ጉለቶች በመለየት በቀጣይ በተቀናጀ መልኩና ችግሮች ባረመ ሁኔታ በትኩረት መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል ።
የእዣ ወረዳ ግብርና ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ መቻል ተሰማ በበኩላቸው በወረዳው የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሰረት ያደረጉ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ በማካሄድ የመሬት ሀብቶችን በመጠቀም በዘርፉ ውጤታማ የሆነ ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ።
ሀላፊው አክለውም እየደረሰው ያለውን የመሬት መጎሳቆል እንዲሁም በመሬት ዙሪያ የሚነሱ አስተዳደራዊ ችግሮች በማስወገድ በጥናት ላይ የተመሰረት ዘላቂና ህጋዊ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓትን ለማስፈን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ።
አቶ መቻል አያይዘውም መሬቱ ባዶ ካሳደረ ፡ መሬቱ ላይ በተለያየ መልኩ ጉዳት ሲያደርስ በተለይም ያለአግባብ ባህርዛፍ ሲተከል ፡ ለበለጠ የህዝብ ጥቅም ሲፈለግ ፡ ማንኛውም የመሬት ባለቤት ባለቤትነቱ ወይንም የመጠቀም መብቱ ሊያጣ እንደሚችል ለማህበረሰቡ በሰፊው የማስገንዘብ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል ።
የእዣ ወረዳ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ታገሰ አርጋው እንደተናገሩት ውጤታማ ፡ ህጋዊና ተጠያቂነት ያማከል የመሬት አስተዳደር ስርዓት በመፍጠር መልካም አስተዳደር ማስፈን ይገባል።
እንደ ወረዳው የዚህ ተቋም ዋና ተግባር የሆነው የአርሶአደሩ የይዞታና የመሬት ባለቤትነት መብት ተረጋግጦ ምቹ የሆነ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት በመዘርጋት እንዲሁም መሬት ነክ ክርክሮችን በአግባቡ በመፍታት በገጠር ዘላቂ ልማትና ምርትና ምርታማነ ለማሳደገም ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ ስራም ነው ብለዋል ።
በሁሉም ቀበሌዎች የመሬት አጠቃቀም ኮሚቴዎች በማሟላት ወቅታዊ ውይይቶች እንዲያደርጉ ማድረግ ይገባል ያሉት አቶ ታገሰ በወጣቶችና በልማት ቡድን ሰበብ የወል መሬት መቀራመትና የወል መሬት ላይ አመታዊ ሰብል ከመዝራት ይልቅ ባህርዛፍ መትከል የሚስተዋልባቸው ላይ ፈጣን የሆነ ክትትልና እርማት የሚገባው በመሆኑ በየአካባቢው ያሉት ባለድርሻ አካላት በነቃ ሁኔታ መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል ።
በእለቱም በፅ/ቤቱ ባለሙያ በመሬት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ የሆነ ውይይት የተደረገ ሲሆን ተሳታፊዎቹም በዚህ ስልጠና ግንዛቤአቸውን እንዲያዳብሩ ያገዛቸው በመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ ህጋዊ የሆኑ አሰራሮችን እንዲሰፍንና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅፍ በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንደሚወጡም በአስተያየታቸው ተናግረዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ።






