የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

ይወደረ

====================

ይወደረ
የጉራጌ ብሄር የፈጠራ ባለቤትነት መብት በማረጋገጥ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የገቢ አቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡
አምራቾች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው መንግስት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል ሲሉ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች ጠየቁ።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ በእዣ ወረዳ ጉየና የሰዎ ቀበሌ በይወደረ ስራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች በጎበኙበት ወቅት እንደተናሩት የጉራጌ ብሔር ከሚታወቅባቸው ሀገር በቀል እውቀቶች አንዱ የጋራ ማዕድ ማቅረቢያ ይወደረ ሲሆን እውቀቱ ተጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ መምጣቱን ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ይወደረ” አንድነትና ፍቅርን የሚሰብክ፣ አብሮነትና መተሳሰብን የሚገልጽ ማዕድ በጋራ የሚቋደስበት ሲሆን በመስቀልና በአረፋ እንዲሁም በሰርግና ድግስ ወቅት በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።
ከዚህም ባለፈ የተከበረ እንግዳ ሲገባ ማዕድ ማቅረቢያ በመሆኑ አሰራሩንም ማስተዋወቅ እንደሚገባና በጉራጌ ባህል ልብስ ውስጥ መንጸባረቁ ለምን እንደሆነ ማስገንዘብ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል፡፡
ይወደረን በሚሰራበት ጊዜ ውበቱን ለመጠበቅ የሚጨመሩ ተግባራት -ማህበረሰባዊ ፍልስፍና እንዳላቸውም ወ/ሮ መሰረት ገልጸዋል፡፡
ይወደረ በሚሰራበት ወቅት በጋራ መሆኑና ተግባሩም በትውልድ ቅብብሎሽ እየተሸጋገረ መምጣቱን የገለጹት ኃላፊዋ ይወደረ ከገጠር አልፎ በከተሞች በተለይም በሆቴሎች ጭምር ተፈላጊነቱ በመጨመሩ አዲሱ ትውልድ በዘርፉ በማሳተፍ የገቢ ማስገኛም እንዲሆን ይሰራል ብለዋል፡፡
ይወደረ በጉራጌ ብሄር ያለውን አስተዋጽኦ በማስገንዘብ የፈጠራ ባለቤትነት መብት በማስጠበቅ ተመሳስለው ከሚሰሩ ምርቶችና ሌሎችም ቅሬታዎችን ቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
የእዣ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ የሺነሽ ተካ በበኩላቸው በእደ ጥበብ ውጤት ለተሰማሩ አካላት የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የገበያ ትስስር በመፍጠር ስራዎችን የማስተዋወቅ ተግባር እንደሚከናወንም ገልጸዋል፡፡
በእዣ ወረዳ ጉየነሰ የሰየ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወጣት ግጥም ብርሃኑና እናቷ በይወደረ ስራ ተሰማርተው ኑሯቸው እየመሩ እንደሚገኙ ነግረውናል።
ወጣት ግጥም ከእናቷ ያገኘችውን እውቀት በመጠቀም ጥራት ያለው ውብና ማራኪ ይወደረ በመሰራት ለገበያ የምታቀርብ ሲሆን በምታገኘው ገቢ ቤተሰቦቿን እየረዳች መሆኗን ተናግራለች።
እናቶች እውቀታቸውን ለተተኪው ትውልድ በማሸጋገር ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
የ”ይወደረ” ግብዓቶችን በጥንቃቄ በማዘጋጀት ይወደረ ሰርተው ለገበያ እንደሚያቀርቡ የተናገሩ ሲሆን ምርቶቻቸው በሚፈለገው ጊዜና መጠን መሸጥ እንዲችሉ በመንግስት በኩል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡