
*****================*******
ጀፎረ”/ጀፎሮ/:- የጉራጌዎች ውብ ስፍራ
ጀፎረ ውብ፣ ፅዱና ማራኪ በአባቶች ባህላዊ እውቀትና ጥበብ የተከሸነ ሰፊ አረንጓዴ ጎዳና፤ በግራና በቀኙ በልምላሜያቸው ተውበው በሚታዩ እፀዋቶች የታጠረ፤ ሳቢና ማራኪ በሆኑ በባህላዊ እደ ጥበብ በተሽቆጠቆጡ ቤቶች የታጀበ፤ በየመሃሉ ላይ እንደ ሊባኖስ ዝግባ የገዘፉ ዛፎች ያሉት፣ ወደ መንደሩ ለሚገባ ሁሉ ለአይምሮ እፎይታን፣ ለነፍስ ደግሞ እርካታን የሚያጎናፅፍ የጉራጌዎች ልዩ ስፍራ ነው።
ጀፎረ በጉራጌ ማህረሰብ ዘንድ ልዩ ታሪክ እንዳለው ይነገርለታል። ጀፎሮ አገልግሎቱ ሁለገብ ነው። ለመንደሮች ውበት መላበስ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
ጀፎረ ማለት የመንደር ወይም የጎጥ ነዋሪዎች የጋራ መጠቀሚያ፣ መተላለፊያ፣ መግቢያ እና መውጫ፣ ሰፊ መሰብሰቢያ፣ ጠዋት ከብቶች ከመሰማራታቸው በፊት ማታ ደግሞ ወደ ቤታቸው ከመግባታቸው በፊት ለማቆሚያነት የሚያገለግል የጋራ ስፍራ ማለት ነው።
ጀፎረ የጎኑ ስፋት 100-150 ሜትር፣ ርዝመቱ በመሃል የሚያልፍ ገደል፣ ደን፣ ወንዝ እስከሌለ ድረስ ሳይቋርጥ ይቀጥላል። ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የሚለካው በዘፈቀደ ሳይሆን በባህሉ በተመረጡ አባቶች ወይም “የዥር ዳነ” የመሬት ልኬት ዳኞች አማካኝነት መሆኑን የዘርፉ አጥኚዎች ይናገራሉ።
የጉራጌ ማህበረሰብ ለጀፎሮ ትልቅ ትኩረት ከመስጠቱ የተነሳ ጀፎሮ ላይ የተተከለ የዛፍ ቅርንጫፍ፣ አፈር ወይም ሌሎችንም ነገሮች ይዞ ወደ ግል ቤት ማስገባት ክልክል ነው።
ጀፎሮ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች አሉት። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል:- ሰው ሲሞት የለቅሶ ስነስርዓት ይከወንበታል፤ ሰርግ ሲኖር የሙሽሪትና የሙሽራው አጃቢዎችና ዘመዶች በባህላዊ ዘፈን በማጀብ ይሞጋገሱበታል፤ ባህላዊ የእርቅ ስነስርዓት ይከናወንበታል፤ ህፃናት ይጫወቱበታል፤ በቅሎና ፈረስ ይገራበታል፤ ወጣቶች የገና ጨዋታ ይጫወቱበታል፤ ወንዶችና ሴቶች የደቦ ስራ ለመስራት ቁጭ ብለው ይመካከሩበታል፤ በመስቀል በዓል አዛውንቶች፣ ጎልማሶች እና ወጣቶች በደመራው ስነስርዓት ላይ ተሰብስበው ይመራረቁበታል፤ አባቶች ባርጩማቸውን ይዘው በመውጣት ንፁህ አየር ይቀበሉበታል።
ጀፎረ ለከብቶች መዋያነትም ያገለግላል። በተለይ በክረምት ወራት ከሰኔ እስከ መስከረም የግርጌ ሳር ከከብቶች መብልነት አልፎ ለቤት ክዳን መክደኛነት እስኪደርስ ድረስ እንደማስተንፈሻ ግልጋሎት መሰጠት ሌለኛው የጀፎሮ ተጨማሪ ጠቀሜታው ነው።
በጉራጌ ብሄረሰብ እያንዳንዱ የመንደሩ ነዋሪ ጀፎሮን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት አለበት። የመንደሩ ማህበረሰብ በዘመቻ መልክ በመውጣት በባለቤትነት ስሜት ጀፎሮን ያፀዳል።
የጀፎሮ መኖር ለእንሰት ተክል እድገት፣ ለቡናና ለሌሎች የጓሮ አትክልት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው። በተለይም ከብቶች ጀፎሮ ላይ ስለሚሰማሩ እነዚህ የጓሮ አትክልቶች በከብቶች እንዳይበሉ ያደርጋል።
በመሆኑም ጀፎሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በመረዳት በተለይ ወጣቱ አባቶች ጠብቀው ያቆዩልንን ሀብታችንን በመንከባከብ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በመወጣት እንዲህ አይነቱን ውብ ባህላችንን እንጠብቅ መልዕክታችን ነው።







