የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

በጉራጌ ዞን የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ የ2ኛ ቀን ፈተና

============

በጉራጌ ዞን የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ የ2ኛ ቀን ፈተና የዞኑ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ት/ቢሮ የትምህርት ልማት ዘርፍና የቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ እና የዞኑ ት/ት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማርያም ሶር ገረፋ ት/ቤት ተገኝተው አስጀምረዋል።
በዞኑ ፈተናው በሁሉም ጣቢያዎች በጥራት ከኩረጃ ነፃ በሆነ ሁኔታ እየተሰጠ እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ት/ቢሮ የትምህርት ልማት ዘርፍና የቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ የ8ኛ ክፍል የ2ኛ ቀን ፈተና ሲያስጀምሩ እንዳሉት ተዘዋውረው እንዳዩት ፈተናው ሂደቱን ጠብቆ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው።
በፈተና ሂደቱ ተማሪዎች ያለምንም ኩረጃ በራሳቸው ጥረት ተረጋግተው እየተፈተኑ መሆናቸውን፣ ፈታኝ መምህራን፣ ሱፐርፋይዘሮችና የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጡ መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
ለዚህም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በተሻሉ መምህራን የቲቶሪያል ትምህርት በአካልና በቪዲዮ በመስጠት ተማሪዎች ለፈተናው ብቁና በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲያዳብሩ በትኩረት መሰራቱን አቶ አስከብር ጠቁመዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ የዛሬ ፈተና ሲያስጀምሩ እንደገለጹት ክልል አቀፍ ፈተናው የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ከሌላ ጊዜ በተለየ ትኩረት እየተሰጠ ነው።
ኩረጃ ለማስቀረት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በዩኒቨርስቲና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች በክላስተር ማዕከል መሰጠቱ በራሳቸው የሚተማመኑ እውቀት ያላቸው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አቶ ክብሩ ገልጸዋል።
አክለውም በዞኑ 326 ትምህርት ቤቶች ላይ ከ25 ሺህ በላይ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን ተረጋግተው እየተፈተኑ መሆኑን ጠቁመዋል።