






========በጉራጌ ዞን የወዲቶ ፣ የዳርቻ እና የጎራ ከገጠር አገልግሎት ማእከል በመውጣት በሀገር አቀፍ ደረጃ የከተሜነት መመዘኛ መስፈርት እውቅና ማግኘታቸውና የቦሌ ፣የፌቅጠረቅ እና የቦዠባር ከተሞች የፈርጅ ለውጥ ማግኘታቸው የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ።።
ከተሞች ወደተሻለ ደረጃ በማሸጋገር እውቅና መስጠትና የፈርጅ ለውጥ ማድረግ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆኑም ተገልጿል ።
የመምሪያው ምክትል እና የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ዩኒት ኃላፊ ወ/ሮ ሸሚማት ለሻድ በዚህ ወቅት እንዳሉት በዛሬው እለት በቸሀ ወረዳ የወዲቶ ፣ በእዣ ወረዳ የዳርቻ እና በገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ የጎራ አካባቢዎች ከዚህ በፊት ከነበሩበት ከገጠር አገልግሎት ማእከል በመውጣት በሀገር አቀፍ ደረጃ የከተሜነት እውቅና አግኝተዋል።
ይህም የዞናችን ከተሞች 37 ከነበሩበት ወደ 40 መድረሳቸው አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በጉመር ወረዳ የቦሌ ፣በቸሀ ወረዳ የፌቅጠረቅ እና በእዣ ወረዳ የቦዠባር ከተሞች ከፈርጅ 5 ወደ ፈርጅ 4 ለውጥ በማድረጋቸው የፈርጅ ለውጥ ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል ነው ያሉት።
የከተሞች እድገት እንዲፋጠን ፣ውብና ለኑሮ አመቺ እንዲሆኑ ህገ ወጥነትን ለመከላከል ከተሞች በማስተር ፕላን መመራት የግድ ይላል ያሉት ወ/ሮ ሸሚማት “ፕላን ለከተሞች ህይወት በመሆኑ” በአፋጣኝ ወደተግባር እንዲገባ አሳስበዋል።
ይህ ማድረግ ደግሞ ምቹ ከተሞች ለትውልድ ማስተላለፍ ማለት መሆኑ አስገንዝበው ከተሞች ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ፣ እውቅና መስጠትና የፈርጅ ለውጥ ማድረግ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑ ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።
ማህበረሰባችን ለከተሞች እድገት ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው።በመሆኑም ይህ ልምድ የዞናችን ከተሞች በፍጥነት ለማድግና ሌሎች ከተሞች የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ እድል ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።
አባቶቻችን ለዘመናት ጠብቀው ያስቆዩልን ጀፎረን በመጠበቅ በከተሞች አካባቢም ከኮሪደር ልማት ጋር አቀናጅቶ መስራት ይገባል ሲሉ ወ/ሮ ሸሚማት ተናግረዋል።
የመምሪያው ምክትል እና የመሬት ማኔጅመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ሀ/ማረያም በበኩላቸው ከተሞች በወጣላቸው ፕላን መሰረት መመራት በተለይ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ተያያዥ ድርጊቶችን ከመከላከል አንጻር ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
ስለሆነም የከተሞች እድገት እንዲፋጠን የፕላን አተገባበር ላይ በትኩረት እንዲሰራበት አቶ ታሪኩ ገልጸዋል።
አቶ ክንፈ ሀብቴ የመምሪያው ምክትል እና የማስፈጸም አቅም ግንባታ እና የመሰረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ሲሆኑ ፕላኑ የህብረተሰቡ የዘመናት ጥያቄ የመለሰ እና የከሞች ቀጣይ የመልማት ፍላጎት የሚያሳካ ነው።
የዞኑ ማህበረሰብ ከተሞች እንዲለሙ ሀብት በማሰባሰብ ፣ጉልበቱና ሀሳቡን በማዋጣት እያደረገ ያለው ተሳትፍ አበረታች ሲሆን ቀጣይም የህብረተሰቡና የመንግስት አቅም አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚገባ አስታውቀዋል።
በርክክብ ወቅቱ የተገኙት አካላት በበኩላቸው እነዚህ ከተሞች ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማድረግ፣በቅርብ ካሉ ትላልቅ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር እና ህዝቡን በማሳተፍ ቀጣይ ለተሻለ የፈርጅ እድገት ማዘጋጀት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የዞኑ ከተሞች በባለቤትነትና በእኔነት ስሜት በመምራት ከተሞቻችን ወደተሻለ ከፍታ ለማድረስ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል።







