






በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ነቆ ( የልጃገረዶች በዓል) በወረዳው ኮኬራ ቀበሌ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።
ጥር 30 /2018 ዓም
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በበዓሉ እለት እንደተናገሩት ባህል ቋንቋ የአንድ ማህበረሰብ ማንነትን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ቁልፍ መሳሪያ ሲሆን በዞናችን እንዲሁም በወረዳችን የጠፉና በጊዜ ሂደት ደብዝዘው የነበሩ ባህሎችና እሴቶች እንዲጎለብቱ ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
በተለይም የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ በማድረግ እንዲሁም መልካም እሴትና ዲሞክራሲ መገለጫ የሆኑ ለሴቶች ክብርና ቅድሚያ የሚሰጥ የስልጣኔ ምልክት የሆነው አንትሮሸት ( የእናቶች ቀን)፡ ነቆ (የልጃገረዶች በዓል) ካለፉት 3ዓመታት ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲያንሰራሩና አለም እንዲያውቋቸው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ጨምረው ተናግረዋል ።
በዛሬው እለትም የተከበረው ነቆ ( የልጃገረዶች በዓል ) ከጥንት ጀምሮ የነበረ በወረሃ ጥር በየአመቱ የሚከበር በተለይም ሴት ልጃ ገረዶች ከእኩዮቻቸው ጋር በጋራ በየአካባቢያቸው ባለው እልፍኝ በመሰባሰብ ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ምግብ መጠጥ እንዲሁም ቁሳቁስ ከቤተሰብ ፡ ከአካባቢና ከግለሰብ በመጠየቅ ነፃነታቸውን ጠብቀው በታላቅ ድምቀት እንደሚያከብሩትና ማህበራዊ ግንኙነታቸውም እንደሚያጠናክሩበትም አቶ ዘውዱ አብራርተዋል።
ስለዚህም የተሟላ ብልፅግና ለማረጋገጥ ወሳኝ የሆነው የማህበራዊ ልማት ትልሞቻችንና የማህበረሰቡ ቁልፍ እሴቶች ማበልፀግ ወሳኝ መሆኑን ተገንዝበን በየደረጃው ያለው አካል ሀላፊነቱ መወጣት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል ።
የእዣ ወረዳ ባህል ቱሪዝም ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ በለጠ ሳህሌ በበኩላቸው የሴቶች ዲሞክራሲ ነፃነት ማሳያ የሆነው ነቆ (አስተሪዮ) የልጃገረዶች በዓል አንዱ ሲሆን ይህም በፈረንጆግ ማረች 8 እና የመሳሰሉት ባልታሰቡበት ዘመን ጉራጌ አስቀድሞ ለእናቶችና ለልጃገረዶች ክብር የሰጠ ታላቅ ማህበረሰብ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል ።
ነቆ የማህበረሰቡ ካለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በተጨማሪ ልጃገረዶች ነፃነታቸውን የሚያውጁበት ፡ የሚገናኙበት ፡ የሚተያዩበት ፡ አብሮነታቸውን የሚያጠናክሩበትና ለወደፊቱ ተስፋ የሚሰንቁበት በዓል ነው ያሉት ሀላፊው ከዚህም በተጨማሪ ሴቶች በራሳቸውን በመተማመን ብቃታቸው ከፍ የሚያደርጉበት እና በቤተሰብ ስጦታ የሚቀበሉበት እርስ በርስ መስተጋብር የሚፈጥሩበት በመሆኑ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል ።
ነቆ ( የልጃገረዶች በዓል) ልጃገረዶች በየአካባቢያቸው በተለያዩ ስራዎች ሲደክሙ የነበሩበትን የሚያርፉበት ፡ የሚጨዋወቱበትና የሚዝናኑበት ነው ያሉት አቶ በለጠ ይህ አኩሪ እሴት ከጊዜ ወደ ግዜ በቴክኖሎጂ ፡ በአለም አቀፍ የባህል ወረራና በሌሎችም ምክንያቶች እየቀዘቀዘ መምጣቱን የጠቆሙት ሀላፊ ይህንን መቀዛቀዝ በዞኑ ወይንም በወረዳው መንግስት እንዲያንሰራራ ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ መከበሩን ገልፀዋል።
የነቆ በዓል በምንም አይነት መልኩ ከሃይማኖታዊ ስርዓት ጋር ግንኘነት የለውም ያሉት ሀላፊው መላው ማህበረሰቡ ይህንን ተገንዝቦ ባህሉን ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል ።
ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየትም መንግ ግስት ቀድሞ ትልቅ ትርጉም የነበራቸውን በመጥፋት ላይ የነበሩ አኩሪ ባህላዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን እየሰራ ያለው ስራ እጅግ የሚደነቅና በሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋልም ብለዋል ።
በዓሉም እለቱን በማስመልከት በድራማና ጭውውት ፡ በባህላዊ ጭፈራና በሌሎችም ተያያዥነት ባላቸው ኩነቶች በድምቀት ተከብሯል ።






