የጉራጌ ዞን ትምህርት ሴክተር ዛሬም ከክልሉ ካሉ መዋቅሮች በትምህርት ተግባራት አፈፃፀም በአንደኝነት ደረጃ አጠናቋል!!

ጥቅምት 03/2018 ዓ•ም (አገና)

“የትምህርት ጥራት ለሁለንተናዊ ብልጽግና”በሚል መሪ ሀሳብ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ሴክተር የ2017 ትምህርት ዘመን ጉባኤ በወራቤ ከተማ ተካሂዷል።

በጉባኤው ማጠቃለያ በተደረገ የእውቅናና ሽልማት ፕሮግራም የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ በአጠቃላይ አፈፃፀም ከክልሉ በአንደኝነት ደረጃ አጠናቋል!!

መምሪያ በ2017 በተመዘገበው የተማሪዎች ውጤት፣በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ አፈፃፀም፣ በመማሪያና ማስተማሪያ መፅሀፍ አቅርቦት፣ በመምህራን ልማት እና ምዘና ስራዎች፣በትምህርት አመራር ሪፎርም፣በትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻልና በሌሎችም 10 መስፈርቶች በመወዳደር በ1ኛ ደረጃ አጠናቀዋል።

እውቅናውን አስመልክተው የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማሪያም ባስተላለፉት መልዕክት፣ የዞናችን ህዝብ የትምህርት ጥቅሙ ቀድሞ የተረዳና የገበው ህዝብ ከመሆኑ የተነሳ ከዚህ ቀደም ለትምህርት ብሎ አካባቢው ጥሎ ከመሰደድ ጀምሮ ረጃጅም ኪሎ ሜትሮችን ይጓዝ እንደነበር አስታውሰው፣ ዛሬ ላይ ይሄንን ችግር ቢቀረፍለትም ውጤታማ ከመሆን አንፃር ሰፊ ስራ ይቀረናል ብለዋል!!

እነዚህና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የዞኑ መንግስት ከህብረተሰቡ፣ከአጋር ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ያሉት ኃላፊው፣አማርድ አካዳሚም ሆነ ዛሬ የተመዘገው የእውቅና ውጤት በዚሁ ትብብር የመጣ ነው ብለዋል!!

ህዝባችንን ለመለወጥ ብለን በሰራነው ስራ የተሰጠን እውቅና ያበረታናል ያሉት ኃላፊው ፣በቀጣይም አጠናክረን በመቀጠል የጉራጌ ህዝብ በትምህርት ዘርፍ ውጤታማና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል።

በመጨረሻም አቶ መብራቴ ወ/ማሪያም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ፣ለውጤቱ መሳካት አስተዋፅዎ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ያመሰገኑ ሲሆን፣ በተለይም የዞኑ አስተዳደር ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠቱና ተገቢውን ድጋፍና ክትትል በማድረጉ፣ የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ጽፈት ቤት ጠንካራ የትምህርት አደረጃጀት ከመፍጠርም በላይ ያልተቋረጠ ክትትልና ድጋፍ በማድረጉ፣ በዞኑ ላሉ ለሁሉም መምህራን ፣ለወላጆች፣ለተማሪዎች፣እስከ ቀበሌ ድረስ ላሉ የትምህርት አመራር አካላትና ባለሞያዎች፣ የመምሪያው የማኔጅመንት አባላትና ባለሞያዎች፣ የወረዳና ከተማ አመራሮች፣በዞኑ በግል በትምህርት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች፣የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ፣ በዞኑ በትምህርት ዘርፍ እያገዙ ላሉ ባለሃብቶችና የበጎ አድራጎት ማህበራት፣ ለጉልባማ፣ ለኢትዮጲያ ቀይ መስቀል ማህበር አመስግነዋል!!

መረጃው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ነው።

“ሰያ” ኢንተርናሽናል ወርልድ ቴኳንዶ ክለብ ለበርካታ ጊዜ ሲያሰለጥናቸው የቆየውን አዲስና ነባር ተማሪዎች በአገና ከተማ ኬሮድ አዳራሽ አስመረቀ።

=========================================

“ሰያ” ኢንተርናሽናል ወርልድ ቴኳንዶ ክለብ ለበርካታ ጊዜ ሲያሰለጥናቸው የቆየውን አዲስና ነባር ተማሪዎች በዛሬው እለት በአገና ከተማ ኬሮድ አዳራሽ  አሰስመረቀ።
ወጣቱ ትውልድ በስነ-ምግባር የታነፀና ጊዜው ያለአግባብ እንዳይባክን እንዲዚህ አይነት የስፖርት ክለቦች ሚናቸው የጎላ ነው ።
በዋና አሰልጣኝ ሳቦም ሰይፈ መካ የሚመራው ይህ ቴኳንዶ ክለብ በወረዳው ብሎም በከተማ መስተዳደሩ በስነ – ምግባር እና በስፖርት የታነፁ ወጣቶች በማፍራት ትልቅ ስራ እየሰራም ይገኛል ።
በዚህ የምርቃት ፕሮግራምም የሰርከስ ትዕይንት : ኤሮቢክስና የተለያዩ የቴኳንዶ ትርኢት ለተመልካቹ ቀርቧል ።

ውጤታማ ፡ ህጋዊና ተጠያቂነት ያማከል የመሬት አስተዳደር ስርዓት

 

 

ነሀሴ 16/2015 ዓ.ም

==============================
ውጤታማ ፡ ህጋዊና ተጠያቂነት ያማከል የመሬት አስተዳደር ስርዓት በመፍጠር መልካም አስተዳደር ማስፈን እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ መሬት አስተዳደር ፅ/ቤት ገለፀ ።

በወረዳው የመሬት አስተዳደር እና የመረጃ ስርዓትን ማዘመን ላይ ትኩረት ያደረገ በካልም ላንድ ፕሮጀክት ድጋፍ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል ።

በእለቱም የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ እንደገለፁት እንደ ወረዳው በገጠር መሬት ላይ የህግ ማዕቀፎች ተግባራዊ በማድረግ ጠንካራ የመሬት ስርዓት ለማስፈን የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አመላክተዋል ።

በተለይም የወል መሬት አጠቃቀም በተመለከተ በቀበሌ ላይ ያሉትን አንዳንድ ችግሮች በቶሎ እንዲቀረፉ የዚህ ባለድርሻ አካል ሚናው የጎላ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ለዚህም ጥራት ያለው መረጃ በአግባቡ በማደራጀትና አጣርቶ ለሚመለከተው አካል በመስጠት እንዲሁም በእርሻ መሬት ላይ የባህር ዛፍ ችግኝ እንዳይተከል በመቆጣጠርና በማስገንዘብ የተቀናጀ ጠንካራ ስራ መስራት ይጠይቃልም ብለዋል።

በቀጣይም በቀበሌ ደረጃ የተዋቀሩ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ኮሚቴዎች በአዋጁ መሰረት በየአካባቢያቸው አስፈላጊውን መረጃዎች ማደራጀት ይገባቸዋል ያሉት አቶ ዘውዱ በተለይም በወል መሬት አስተዳደርና ሌሎችም መሬቶች ባላስፈላጊ መልኩ ከመጠቀም ጋር እየተስተዋሉ ያሉትን ጉለቶች በመለየት በቀጣይ በተቀናጀ መልኩና ችግሮች ባረመ ሁኔታ በትኩረት መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል ።

የእዣ ወረዳ ግብርና ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ መቻል ተሰማ በበኩላቸው በወረዳው የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሰረት ያደረጉ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ በማካሄድ የመሬት ሀብቶችን በመጠቀም በዘርፉ ውጤታማ የሆነ ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ።

ሀላፊው አክለውም እየደረሰው ያለውን የመሬት መጎሳቆል እንዲሁም በመሬት ዙሪያ የሚነሱ አስተዳደራዊ ችግሮች በማስወገድ በጥናት ላይ የተመሰረት ዘላቂና ህጋዊ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓትን ለማስፈን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ።

አቶ መቻል አያይዘውም መሬቱ ባዶ ካሳደረ ፡ መሬቱ ላይ በተለያየ መልኩ ጉዳት ሲያደርስ በተለይም ያለአግባብ ባህርዛፍ ሲተከል ፡ ለበለጠ የህዝብ ጥቅም ሲፈለግ ፡ ማንኛውም የመሬት ባለቤት ባለቤትነቱ ወይንም የመጠቀም መብቱ ሊያጣ እንደሚችል ለማህበረሰቡ በሰፊው የማስገንዘብ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል ።

የእዣ ወረዳ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ታገሰ አርጋው እንደተናገሩት ውጤታማ ፡ ህጋዊና ተጠያቂነት ያማከል የመሬት አስተዳደር ስርዓት በመፍጠር መልካም አስተዳደር ማስፈን ይገባል።

እንደ ወረዳው የዚህ ተቋም ዋና ተግባር የሆነው የአርሶአደሩ የይዞታና የመሬት ባለቤትነት መብት ተረጋግጦ ምቹ የሆነ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት በመዘርጋት እንዲሁም መሬት ነክ ክርክሮችን በአግባቡ በመፍታት በገጠር ዘላቂ ልማትና ምርትና ምርታማነ ለማሳደገም ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ ስራም ነው ብለዋል ።

በሁሉም ቀበሌዎች የመሬት አጠቃቀም ኮሚቴዎች በማሟላት ወቅታዊ ውይይቶች እንዲያደርጉ ማድረግ ይገባል ያሉት አቶ ታገሰ በወጣቶችና በልማት ቡድን ሰበብ የወል መሬት መቀራመትና የወል መሬት ላይ አመታዊ ሰብል ከመዝራት ይልቅ ባህርዛፍ መትከል የሚስተዋልባቸው ላይ ፈጣን የሆነ ክትትልና እርማት የሚገባው በመሆኑ በየአካባቢው ያሉት ባለድርሻ አካላት በነቃ ሁኔታ መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል ።

በእለቱም በፅ/ቤቱ ባለሙያ በመሬት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ የሆነ ውይይት የተደረገ ሲሆን ተሳታፊዎቹም በዚህ ስልጠና ግንዛቤአቸውን እንዲያዳብሩ ያገዛቸው በመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ ህጋዊ የሆኑ አሰራሮችን እንዲሰፍንና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅፍ በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንደሚወጡም በአስተያየታቸው ተናግረዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ።

በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የበለፀገው ezhaguraghe.gov.et የተሰኘ ዌብሳይት በዛሬው እለት ተመረቀ።

ነሀሴ10/2015 ዓም

===============================

በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የበለፀገው ezhaguraghe.gov.et የተሰኘ ዌብሳይት በዛሬው እለት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል ።

ይህም ዌብሳይት የበለፀገው በእዣ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፅ/ቤት ፡ በአገና ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ እና በእዣ ወረዳ አስተዳደር ትብብር አማካኝነት መሆኑን ተጠቁሟል።

በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ የተገኙ የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ሀላፊ አቶ ደምስ ገብሬ እንደገለፁት ተቋሙ የተቋቋመበት ዋና አላማ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በማልማትና በሁሉም ስፍራ በስፋት በመጠቀም የሳይንስ የሳይንስና ፈጠራ ስራዎችን በማበረታታት ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን ፈልቀው የህብረተሰቡ ኑሮ እንዲሻሻል ነው ።

የእዣ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተቋምም በዞኑ ካሉ መዋቅሮች ግንባር ቀደም ነው ያሉት ሀላፊው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ይህም ዌብሳይት መልማት መቻሉ እንደዞኑ ብሎም እንደወረዳው ዘርፈብዙ ጥቅም ያለው ስለሆነ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በበኩላቸው በወረዳው ደረጃ ዘርፈብዙ ጥቅም ሊሰጥ የሚችለውን ዌብሳይት በልፅጎ ለምርቃት መብቃቱ እጅግ የሚያስደስትና ዓለም የደረሰችበት የቴክኖሎጂ እድገት ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ትልቅ እድል የፈጠረነው ብለዋል።

ዌብሳይቱም እንደ ወረዳው የሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲያዊ ግንባታ ስራዎች በቀላሉ ለህብረተሰቡ ብሎም ለመላው አለም በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ ያለው ፋይዳ በጣም ከፍተኛ እንደሆነም ዋና አስተዳዳሪው አመላክተዋል።

በቀጣይም ዌብሳይቱ ደህንነቱ የተረጋገጠና አሳታፊ እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ ይገባል ያሉት አቶ ዘውዱ መረጃን በጥራትና በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ ሁሉም ተቋማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትብብርና ተሳትፎ የሚሻ በመሆኑ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የእዣ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሪት ራሂማ ሙህታጅ ተቋሙ ቴክኖሎጂን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል እንደ ወረዳው የተለያዩ ባለድርሻ የሆኑ ተቋማት በማሳተፍ ezhaguraghe.gov.et የሚል የዶሜን ስም ያለው ዌብሳይት በማልማት እነሆ በዛሬው እለት ለምርቃት በቅቷልም ብለዋል።

ሀላፊዋ አክለውም ዌብሳይቱ በመልማቱ world widweb በወረዳው ዶሜን ኔም አማካኝነት አክሰስ የምናደርገው የትኛውም ወረዳዊ መረጃዎች በማስቀመጥ በማንኛውም አለም ላይ ያለው አካል ተደራሽ መሆን የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል ።

ይህ ዌብሳይት በዋናነትም በወረዳው የመንግስት ተቋማት በልማትና መልካሞ አስተዳደር ፡ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያከናወኗቸው ስራዎች ለማስተዋወቅ ፡ የወረዳው አጠቃላይ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦች ፡ ታሪካዊ ፡ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ለአለም በማስተዋወቅ እና ወረዳው የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ለማድረግ ያስችላል ያሉት ሀላፊው እንዲሁም ወረዳዊ የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅ እና ባለሀብቱ ወደ ወረዳው ለመሳብ ዌብሳይቱ እጅግ ያግዛልም ብለዋል።

ሌላው በወረዳው ያሉ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸው በቀላሉ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጥቅሙ የጎላ ነው ያሉት ወ/ሪት ራሂማ በአጠቃላይ እንደ ወረዳ የሚሰጡ አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ማግኘት እንዲቻል ዌብሳይቱ ጠቃሚ ነው ብለዋል።

ዌብ ሳያቱ ያበለፀገው የአገና ኮንንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ አሰልጣኝ መምህር ስንታየሁ ፈለቀ አጠቃላይ ስለዌብሳይቱ ሁኔታና አጠቃቀም ላይ ሰፊ ገለፃ ያደረገ ሲሆን ዌብሳይቱም የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን መምሪያ ባወጣው መሰረትየተሰራ መሆኑንም አመላክቷል።

ተሳታፊዎቹም በሰጡት አስተያየት ይህ ዌብ ሳይት መልማቱ እጅግ የሚያስደስትና የሚበረታታ ተግባር ሲሆን በወረዳው የሚገኙ አጠቃላይ የየተቋማት መረጃዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በዚህ ተጠቃሚ ለመሆን አስፈላጊውን ጥረት እናደርጋለንም ብለዋል ።
በመጨረሻም የአገና ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪሪያሪያል ኮሌጅ ከወረዳው ሳይንስና ኢንፎርሜሽንእና ከወረዳው አስተዳደር ዌብሳይቱ ርክብክብ አድርገዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው ።

 

መስከረም 2016ዓ.ም የመስቀል በዓል ዝግጅትና አከባበር በጉራጌ በከፊሉ!!

መስከረም 2016ዓ.ም
የመስቀል በዓል ዝግጅትና አከባበር በጉራጌ በከፊሉ!!

የጉራጌ ብሔረሰብ በድምቀት ከሚያከብራቸው በዓላት መካከል ትልቁና ዋነኛው የመስቀል በዓል ነው፡፡

የመስቀል በዓል በጉራጌ ብሔረሰብ ያለው ማህበራዊ ፋይዳ ትልቅ ነው ። ዓመቱን ሙሉ ተለያይተው የኖሩ ቤተሠቦችና ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ የሚጠያየቁበት፣ ማህበራዊ ችግሮቻቸው የሚፈቱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ በጋብቻ የተሳሰሩ ቤተሠቦች የሚጠያየቁበት፣ በጥል የተለያዩ ባልና ሚስቶች የተጣሉ ሠዎች የሚታረቁበት፣ እዳ የሚሠረዝበትና በዳይና ተበዳይ ይቅር የሚባባሉበት በዓል ነው፡፡

ወጣቶችና አዛውንት ደመራ ለማብራት በወጡበት በእድር ደንቦች በአካባቢ ልማት፣ በግብርናና ንግድ ስራዎች ላይ የሚመክሩበት፣ ወጣቶች በአባቶች የሚመረቁት፣ ጎልማሶች ከአባቶች ኃላፊነት የሚረከቡት፣የወላድ ማህፀን የሚባረከው፣ ሟርተኞች የሚረገሙት በዚሁ በዓል ነው፡፡

ወላጆች ለበዓሉ የተዘጋጀን ሰንጋ ከፊታቸው አቁመው ሻኛውን በመዳሰስ ትውልዱን ይመርቃሉ /ይባርካሉ/፤ ለአገር ሰላምና ብልፅግና ፈጣሪያቸውን በፀሎት ይለምናሉ፡፡ በጐረቤት እና በአካባቢ ያለን ችግረኛ የሚያስቡበት፣ ለወለደች አራስ የሸሉዳ ስጋ፣ ለተገረዙ ልጆች ጭቅና ስጋ የሚሰጡበት በመስቀል በዓል ነው፡፡

በጥቅሉ የመስቀል በዓል አጀማመር መሰረት የሆነዉ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል መገኘት ሲሆን በአመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መከበር የጀመረዉ በ4ኛ ክፍለ ዘመን (327ዓ.ም) በንግስት እሌኒ የአገዛዝ ዘመን ጀምሮ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

ለመስቀል በአል የሚደረግ ዝግጅት ብሔረሰብ ዘንድ ትልቅ በዓል እንደመሆኑ ዝግጅቱም እንዲህ ከበድ ያለ ነዉ ፡፡
የመስቀል በዓል ዝግጅት የሚጀምረዉ መስቀል በተከበረበት ዓመት በዓሉ እንደተጠናቀቀ ለሚቀጥለዉ አመት የመስቀል በዓል በማሰብ ነዉ ፡፡

በተለይ ከትዉልድ ቀዮአቸዉ ርቀዉ የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች ከቀን ሰራተኛዉ እስከ ደሞዝተኛዉ ከሱቅ በደረቴ እስከ ትልቁ ነጋዴ ለመስቀል በዓል ብለዉ የተለየ ገንዘብ በየጊዜዉ ጣል በማድረግ የሚያጠራቅሙት በበጋዉ ወራቶች ጀምሮ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እናቶችም ለመጪዉ መስቀል በዓል የቅቤ ዝግጅት የሚጀምሩ ገና በዓሉ እንደተጠናቀቀ ሲሆን ዓመቱ ሙሉ የማያቋርጥ የቅቤ ዉጆ/የቅቤ እቁብ /ማጠራቀም ለመስቀል በዓል ዝግጅት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጡት ትክክለኛ ማረጋገጫ ነዉ ፡፡መስቀል ሶስትና አራት ወራት ሲቀሩት ዝግጅቱ እየተጧጧፈ ይሔዳል፡፡

በዚህ ወቅት የስራ ክፍፍሉ በእድሜና በፆታ ተደላድሎ ለሁሉም እንደ አቅሙና ችሎታዉ ይሰጣል ፡፡ ወጣት ወንዶች ለመስቀል በዓል የሚሆን ባህርዛፍ በደቦ ቆርጠዉ በመፍለጥ የወይራ ዛፍ ጉቶ አዘጋጅተዉ ማደራረቅና ከደረቀም በኃላ ቤት አስገብቶ በቆጥ ላይ መደርደር ሲሆን ፣የአባዎራዎች ድርሻ የሚሆነዉ ለእርድ የሚሆኑ ከብቶች ማድለብና ማዘጋጀት ከቤትም ከሌለም አስቀድሞ ገዝቶ ማድለብ እንዲሁም በመስቀል ወቅት በቤት ዉሥጥ ያሉት ከብቶች የሚሰማሩበት ክልክል የሳር ቦታ መከለልና ለተወሰነ ቀናቶች የሚሆን ሳር አጭዶ ማቆየትና ለበዓሉ የሚሆኑ ቢላዎች መግዛት ማስሞረድ የመሳሰሉት ናቸዉ ፡፡

የወጣት ሴቶች የስራ ድርሻ ደግሞ ቤት ማሳመር የተለያ ቀለም ባለቸዉ አፈሮች ቤት መቀባት ሲሆን እማዎራዎች በቅድሚያ እንሰት ፍቀዉ ማዘጋጀት በደቦ አዲስ ጅባ መስራት ወይም መግዛት ያረጁና ያለቁ የቤት ቁሳቁሶች በአዲስ መለወጥ የመስቀል ሚጥሚጣ ከልጆች ጋር ወቅጦ ማዘጋጀት ፈሳሹ ተንጠፍጥፎ የወጣለት የበዓል ቅቤ በተለያ ቅመሞች አሽቶ ማንጠርና ለበዓሉ የሚሆኑ ባህላዊ መጠጦች ማዘጋጀት ዋና ዋና ተግባሮች ናቸዉ፡፡

በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ እና አገና ከተማ አስተዳደር የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ ስርዓት በጠበቅ መልኩ በተለያዩ አድባራት በሰላምና በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

========================

በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ እና አገና ከተማ አስተዳደር የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ ስርዓት በጠበቅ መልኩ በተለያዩ አድባራት በሰላምና በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

የአገና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀብቴ ዘርጋ በጥምቀተ ባህር ተገኝተው ለህዝበ ክርስቲያኑ የበአሉ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደገለጹት የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ ሀይማኖታዊ በዓል በመሆኑ ይህንን ቅርስ ተንከባክቦ በመጠበቅና ለአለም ይበልጥ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ሀብትነቱን ማሳደግ ይገባል።

ከንቲባው አያይዘውም ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉ ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት በፈጣሪ ዘንድ የተወደደና ማህበራዊ ግዴታ እየተወጣን ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው ህብረተሰቡ በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የአከባቢውን ጸጥታ ነቅቶ መጠበቅ አለበት ብለዋል።

በጉራጌ ሀገረ ስብከት የእዣ ወረዳ ቤተክህነት ተወካይና የድረሬ ቅዱስ ገብርኤል ገዳመ ወደብር አስተዳዳሪ መልአከ ፀሀይ ተንሳይ ስራ እንዳሉት የበዓሉ ዋና አላማ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ተነስቶ ወደ ዮርዳኖስ በመውረድ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ በመጠመቅ የአዳም ልጆች የእዳ ደብዳቤያቸውን የቀደደበትና ህዝበ ክርስቲያኑ የመንፈስ ቅዱስ ልጅነት ያገኙበት በአል ነው ብለዋል።

በመሆኑም ህዝበ ክርስቲያኑ ጽድቅ ሊፈጽምና በጽድቅ ሊመላለስ ይገባል ብለዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው ።

ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን

=========================================

የጨረራ ምንነት

ጨረራ(Radiation)

በሞገድ (wave) መልክ  ወይም   በአነስተኛ ልዩ ልዩ ቅንጣቶች(Particles)  ኤነርጂ ከቦታ ወደ ቦታ የሚተላለፍበት መንገድ ነው፡፡

የጨረረ ዓይነቶች

አዮን ፈጣሪ ጨረራ እና  አዮን ፈጣሪ ያልሆኑ  ጨረራ ተብለው  በ2 ይከፈላሉ

1.አዮን ፈጣሪ ጨረራ ማለት  ጨረራ በቁስ (matter) ውስጥ በሚያልፉበት ጊዜ  አዮን መፍጠር የሚችሉ ሲሆኑ

የጋማ፣የቤታ፣ የአልፋ፣  የኒውትሮን   የኤክስሬይ  አዮን ፈጣሪ የሆኑ  የጨረራ ዓይነቶች ናቸው

2.አዮን ፈጣሪ ያልሆነ ጨረራ ማለት ጨረራ በቁስ (matter) ውስጥ ሲያልፉ አዮን የማይፈጥሩ   ሲሆኑ የተለያዩ የራዲዮ ሞገዶች፣  ልዕለ ሃምራዊ፣ ታህተቀይ፣ ብርሃን   ሌዘር  አዮን ፈጣሪ ያልሆኑ የጨረራ ዓይነቶች ናቸው፡፡

የጨረራ መንስዔዎች

በቁስ ውስጥ ጨረራ በሁለት  ቦታ በአቶሚክ ሼል እና በኒዩክሌስ ውስጥ ሊፈጠር ይችላል አተሞች ለመረጋጋት በሚያደርጉት በኒየክሌስ ውስጥ ጨረራ የሚፈጠረው በአተሞች አለመረጋጋት ሲሆን ይህም በአቶም ውስጥ ያለው የፕሩቶን ቁጥር ከኒዩትሮን ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በጣም ከፍ ወይም በጣም ዝቅ ሲል ነው እንቅስቀሴ በቅንጣጢት(Particles)መልክ  እንደ  አልፋ፣ቤታ፣ኒዩትሮን ጨረራ ሞገድ(Electromagnetic Wave) እንደ ጋማ  ጨረራ  ይለቀቃሉ ኤክስሬይ ደግሞ በአቶሚክ ሼል ውስጥ ኤሌክትሮኖች ከአንዱ ሼል ወደ

ሼል በሚያደርጉት ሽግሽግ በሚፈጠር ኤነርጂ ልዩነት ምክንያት ይፈጠራል፡፡

  • የጨረራ ምንጮች

1.በተፈጥሮ የሚገኙ የጨረራ ምንጮች

2.ሰው ሰራሽ   የጨረራ ምንጮች

ተፈጥሮ የጨረራ ምንጮች የሚባሉት  ፀሀይ፣ ከዋክብት፣  በምድር ላይ የሚገኙ ጨረራ አመንጪ ማእድናት  ናቸው

የተፈጥሮ የጨረራ ምንጮች

ዩኒቨርስ ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ ያሉ ናቸው

መጠናቸው ከቦታ ቦታ ከሀገር ሀገር ይለያያሉየ

ጨረራ ጥቅም

በሃይል ምንጩ ዘርፍ

  • በኃይል ምንጭነት፣
  • ለኤሌክትሪክ አቅርቦት
  • የባሕር ውኃን ከጨው ለመለየት
  • ለጠፈር ጉዞና ምርምር
  • በባሕር ላይ ለሚደረግ የመርከብ ጉዞ

የምርምር ማብለያ  (Research Reactors )

¨ በትምህርት ተቋማት ስልጠና ለመስጠት

¨ ለምርምር

¨ በሕክምናና በኢንዱስተሪ ውስጥ የሚያስፈልጉ

¨ ራዲዮ  አይሶቶፖችን ለማቀነባበር

¨ የመሳሪያዎችን ጥራት ለመለካት

በግንባታው ዘርፍ

  • የመንገዶችን
  • የሕንፃ መሰረቶች፣
  • የድልድዮች
  • ጥራትና ደረጃ ለማረጋገጥ ለውኃ እና ማዕድን ፍለጋና ልማት፣

መንገድ  ስራ ላይ   በአይሶቶፕ ሀይድሮሎጂ  የውኃውን ዕድሜ፣መነሻ ቦታና የውኃውን የፍሰት እንቅስቃሴ ለማወቅ አይሶቶፖች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

  • · በኢንዱስትሪ የምርት ጥራትንና የሥራ ሂደቶችን ለመቆጣ(Quality tests, Non-Destructive Tests) -NDT-

ነዳጅ ፍለጋ

በኢንዱስተሪያል ራዲዮግረፊ ተግባር  የኤክስ ሬይና ጋማ ሬይ ጥራትን ለመቆጣጠር  ጥቅም ይሰጣሉ

  • የራዲዮግራፊክ ፍተሻ
  • የቅሪት አካላትን ዕድሜ ለማወቅ
  • የሻንጣና የጭነት  መፈተሻ

ጨረራ በሕክምናው ዘርፍ ያለው ጥቅም

የራጅ ምርመራ

  • የኒዩክሌር ሕክምና
  • የጨረራ ሕክምና

ኒዩክሌር መድኃኒቶች

ጨረራ ጉዳቶች

አዮን  ፈጣሪ ለኾኑ የጨረራ ዓይነቶች አለአግባብ  መጋለጥ በሰው ጤና ላይ በአጭር ጊዜ  የአካል ጉዳትና ሞት፣

ወደ ትውልድ የሚተላለፉ ልዩ ልዩ የጤና ችግሮች

በረጅም ጊዜ ሊከሰት የሚችል ካንሰር ሊያመጣ ይችላል፡፡

አዮን ፈጣሪ  ላልሆኑ የጨረራ ዓይነቶች አለአግባብ  መጋለጥ

በሰው ጤና ጣይ ምርምሮች የሚካኼዱበት ሆኖ የሕዋሶቻችን ሙቀት እንዲጨምር

ለሚያደርግ በረጅም ጊዜ ሊያስከትለው የሚችል ጉዳት ይኖረዋል

የጨረራ ሥነ– ሕይወታዊ ተፅዕኖጨረራው ዓይነት

  • የጨረራው ኃይልና የውስድ መጠን አወሳሰድ

የተጋለጠው አካል(ለጨረራ ያለው ስሜታዊነት)

የጨረራ ውስድ መጠን  የሚያስከትለው ሥነ–ሕይወታዊ ተፅዕኖ የሚወስኑ ምክንያቶች

ጨረራ መከላከልና ደኅንነት መርሆዎች

ICRP እርስ በርሳቸው የሚዛመዱ 3 መሰረታዊ

የጨረራ መከላከልና ደህንነት  መርሆዎች(Principles) ተግባራዊ እንዲደረጉ ይጠቁማል፡፡

እነሱም፣

ጥቅሙና ጉዳቱ ማመዛዘን(Justification)

የጨረራ መጠን በመቀነስ አጥጋቢ ውጤት ማግኘት (Optimization) –ALARA Principle

እናከ ተፈቀደ የጨረራ ውስድ መጠን አለማለፍ(Dose Limitation)  የሚባሉ ናቸው፡፡

ለጨረራ  የምንጋለጥባቸው  መንገዶች

ለጨረራ  የምንጋለጥባቸው  መንገዶች 2 ናቸው፡

ውስጣዊ መጋለጥ   በትንፋሽ  በምግብና ፈሳሽ  በቆሰሉ ወይም በተቆረጡ የቆዳ አካሎች

ውጫዊ መጋለጥ  በጋማ  በራጅ  በኒዩትሮንና በሌሎችም

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ድጋፍ ክትትልና አቅም ግምባታ ዳይሬክቶሬት

ስልክ ፡-0113290735

Email ፡-Edjaworedasitoffice@gmail.com

website፡- Ezhaguraghe.gov.et

Telegram :-የእዣ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽ/ቤጽ( Ezhaworda SIT office )

 

 

 

“ጋበር” የበጎ አድራጎት ድርጅት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መጽሀፍቶችና የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለእዣ ወረዳና ለአገና ከተማ አስተዳደር ማስረከቡ ተገለጸ።

========================================

ጥቅምት 3 /2016ዓ.ም
“ጋበር” የበጎ አድራጎት ድርጅት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መጽሀፍቶችና የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለእዣ ወረዳና ለአገና ከተማ አስተዳደር ማስረከቡ ተገለጸ።
የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከመንግስት ጎን በመሆን ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
የጋበር በጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኮሬ ባዌ መጽሀፍት እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ርክክብ ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት በአካባቢው በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ችግሮችን ያሳሰባቸው የአካባቢው ተወላጆች ጋበር የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት በማቋቋም የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሰራ ይገኛል።
ድርጅቱ በዋናነት አላማ አድርጎ የተቋቋመው በእዣ ወረዳ ያሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን መንግስት ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት የአካባቢው ህብረተሰብ በማስተባበር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችል ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ኮሬ ገለጻ በወረዳው ከ7-12ኛ ክፍል ለሚማሩ ልጃገረዶች በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የመማሪያ መጽሀፍት እንዲሁም ከ9-12 ክፍል ላሉ ተማሪዎች የማጣቀሻ መጽሀፍት ለእዣ ወረዳ እና ለአገና ከተማ አስተዳደር እንዳስረከበም ተናግረዋል።
ድርጅቱ በትምህርት ዘርፍ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የመጽሀፍ ድጋፍ እንዲሁም ቀልጣፋና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ለአገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የህክምና ቁሳቁስ ለማሟላት ከመስራት ባለፈ በሌሎችም ዘርፎች ለመስራት አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ድርጅቱ ከወረዳው አመራርና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይም ድርጅቱ በሚያከናውናቸው ስራዎች ህብረተሰቡና አመራሩ እያደረጉት ያለው ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ጋበር እያደረጋቸው ያሉ መሰል ስራዎች አርዓያነት ያላቸው ተግባራት በመሆናቸው የጉራጌ ተወላጆች በሁሉም አካባቢዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት በመመስረት በአካባቢያቸው የሚስተዋሉ የልማት ስራዎች ክፍተት ለመሟላት መስራት እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጋበር በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ምናሴ እንዳሉት 3 ሺህ 386 የሚሆኑ ማጣቀሻና የመማሪያ መጽሀፍ፣ 3286 የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በዋጋ ሲተመን 5 ሚሊዮን 326 ሺህ 437 ብር ወጪ ተደርጎባቸዋል።
ጋበር የበጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ ከማድረጉ ጎን ለጎን በወረዳውና በከተማው በሚገኙ በ7 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎችና በአገና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ትምህርታቸው ለሚከታተሉ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱንም ገልጸዋል።
ጋበር ከ1-6ኛ ክፍል በወረዳው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተዘጋጁ 15 ሺህ 420 የመማሪያና የመምህር አጋዥ መጽሀፍት ለማቅረብ መጽሀፍቱ ህትመት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ለእነዚህ መጽሀፍት 4 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው ያነሱት ስራ አስኪያጁ ከሚቀጥሉት ጊዜያት ጀምሮ ስርጭቱ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ጋበር እያካናወናቸው ያሉ ስራዎች ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የጋበር የቦርድ አባል ዶክተር እንዳለጌታ ከበደ ጋበር የማህበረሰቡን ችግሮችን በመገንዘንብ እየሰራ ያለው ተግባር ሌሎችም ድርጅቶች በዞኑ መሰል ስራዎች በመስራት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ዶክተር እንዳለ ጌታ አክለውም እንደ ሀገር የወረደው ውጤት ተረድተው ተማሪዎች የተደረገላቸው ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀም ተግተው መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ድርጅቱ በወረዳው ያለው የመጽሀፍ እጥረት በመገንዘብ ከአካባቢው ተወላጆችን ድጋፍ በማሰባሰብ የመማሪያና አጋዥ መጽሀፍት ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
የእዣ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋለም ብዛ በበኩላቸው በወረዳው ያለው የመጽሀፍ እጥረት ችግር ለመፍታት ጋበር ድጋፍ ያደረገላቸው የመማሪያና ማጣቀሻ ብሎም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ መረከባቸውን ገልጸው እነዚህም በቀጣይ ለሁሉም ትምህርት ቤቶች ተደራሽ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
የተደረገው ድጋፍ በአሁን ወቅት የወረደው የተማሪዎች ውጤት ከፍ እንዲል አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑንም አመላክተዋል።
የወረዳ አስተዳደር ጋበር በወረዳው እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን እንደሚያግዝና በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ጋበር ሀገር ተረካቢ ዜጎች ለማፍራት እያደረገው ያለው አርአያነት ያለው ተግባር በዞኑና በሀገር ደረጃ ያሉ መሰል ድርጅቶች በዞኑ በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎች በትምህርት ጥራት ላይ ያለው ችግር ለመቅረፍ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ተማሪ ዮርዳኖስ ይርጋ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ለምለም ታሪኩና ዳንኤል ፉጀ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው።
ተማሪዎቹ በጋራ በሰጡት አስተያየት ጋበር የበጎ አድራጎት ድርጅት ባደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ጠቁመው ይህም ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀም ተግተው እንደሚማሩ ገልጸዋል።
በተለይም በትምህርት ቤቶች የመጽሀፍ እጥረት እንዳለ ገልጸው ጋበር ያደረገው ድጋፍ ችግሩን እንዲቀንስ ከማድረጉም ባለፈ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ያደርጋል ነው ያሉት።
በንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው የሚቀሩና የሚያቋሩጡ ተማሪዎች እንደነበሩ ጠቁመው ይህም ሴት ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸው በመከታተል ለውጥ እንዲመጣ ያደርጋል ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

የእዣ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት የ2015 ዓ.ም ማጠቃለያ የተቋማትና የፈጻሚዎች የእውቅናና ሽልማት ፕሮግራም አካሂዷል ።

===============

መስከረም 25/2016 ዓም
የሲቪል ሰርቫንቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ቀልጣፋና ፍትሃዊ እንዲሆን በማስቻል የተቋማት የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ማጎልበት እንደሚገባ ተገለፀ ።

የእዣ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት የ2015 ዓ.ም ማጠቃለያ የተቋማትና የፈጻሚዎች የእውቅናና ሽልማት ፕሮግራም አካሂዷል ።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በዚህ ወቅት እንደገለፁት የሲቪል ሰርቫንቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ቀልጣፋና ፍትሃዊ እንዲሆን በማስቻልና የሚበጀተው ውስን ሀብት ለታለመለት አላማ እንዲውል በማድረግ የተቋማት የመፈፀምና የማስፈጸም አቅም ማጎልበት ይገባል።

ሲቭል ሰርቫንቱ ከአድሏዊ አሰራር እና ከኪራይ ሰብሳቢነት በፀዳ መልኩ በመስራት ተገልጋዩ ህብረተሰብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ፈጣንና ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ በመስጠት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም ዋና አስተዳዳሪው አመላክተዋል ።

የመንግስት ሰራተኞች ብዙ ውስብስብ ችግሮችና ጫናዎች ቢኖርበትም ህዝቡ ለማገልገልና በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የሰው ሀይል እያደረገም ይገኛል ብለዋል ።

በተቋማት መካከል ያለው የአፈፃፀም ልዩነት ለማቀራረብ እንደ ተቋሙ እየተሰሩ ስራዎች ማጠናከር ያስፈልጋል ያሉት አቶ ዘውዱ አመራሩና ባለሙያው በመቀናጀት በጉለት የተገለፁ ተቋማት ከጉድለታቸው እንዲወጡ የማድረግና ጥሩ አፈፃፀም ያሳዩትን ደግም በተሻለ መልኩ በማጠናከር እንደ ወረዳ ማህበረሰቡን በታማኝነት ማገልገል እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የእዣ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ በለጠ ሳህሌ በበኩላቸው በወረዳው የፐብሊክ ሰርቫንቱን አቅምና ልምድ በመጠቀምና የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

መንግስት በየጊዜው ቀርፆ የሚያወርዳቸው ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና ደንቦችን በማክበርና በማስከበር ረገድ ፐብሊክ ሰርቫንቱ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ያመላከቱት ሀላፊው ሁሉም ተቋማት አደረጃጀቶችን እንደ መሳሪያ በመጠቀምና በማሳለጥ ተግባራትን በተገቢው መፈጸም እንዳለባቸው አብራርተዋል ።

በቀጣይም ሲቪል ሰርቫንቱ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት ሙያዊና የዜግነት ግዴታውን በቅንነትና በታማኝነት ለመወጣት መትጋት አንዳለበትም አቶ በለጠ መልዕክት አስተላልፈዋል ።

በእለቱም የዓመቱ ግንባር ቀደም ተቋም ከሆኑት መካከል የአስተዳደር ፅ/ቤት ምርጥ ተሞክሮ የቀረበ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ የእዣ ወረዳ ፍትህ ፅ/ቤት ግንባቀደም ፈፃሚ ባለሙያ ተሞክሮ በሀላፊዎች የማቅረብና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማትፅ/ቤት የ2015 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል ።

በመጨረሻም በ2015 በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈፃፀም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተቋማትና ፈፃሚዎች የሽልማትና የእውቅና መርሐ ግብር የተካሄደ ሲሆን ከተቋማት 1ኛ አስተዳደር ፅ/ቤት 2ኛ ፍትህ ፅ/ቤትና 3ኛ ፋይናንስ ፅ/ቤት እንደየ ደረጃቸው እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።

በተመሳሳይ በየሴክተሩ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ከ1እስከ 3ኛ የወጡ ሰራተኞች ፡ ከአጠቃላይ ወረዳ ሰራተኞች ከ1እስከ 3ኛ የወጡ ባለሙያዎች ፡ እንደ ወረዳ ከአጠቃላይ ሴቶ ሰራተኞች ከ1እስከ 3ኛ የወጡ ባለሙያዎች ፡ የገጠር ቀበሌ ፈፃሚ ባለሙያዎችና የጤና ባለሙያዎች እና የጋራ አገልግሎት ሰራተኞች ግንባር ቀደሞች የተሸለሙ ሲሆን የእዣ ወረዳ ፋይናንስ ፅ/ቤት ባለሙያ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ፍታኒ የልዩ ተሸላሚ ሆነዋል ሲል የገለፀው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው ።