
አምባ ደን
አምባ ደን የሚገኘው በዌራ ደባነ ቀበሌ ሲሆን, ከዞኑ ዋና ከተማ ከወልቂጤ በ44 ኪ.ሜ እና ከወረዳው ዋና ከተማ አገና በ2 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በስተምስራቅ አቅጣጫ በአስፓልት ዳር ላይ ይገኛል፡፡ የደኑ ስፋት 200 ሄክታር መሬት ይሸፍናል፡፡ ይህ ደን እጅግ በጣም ጥቅጥቅ ያለ እና ነፋሻማ የአየር ንብረት ያለበት, የቱሪስት ቀልብ የሚስብ ተፈጥሮአዊ ደን ነው፡፡ ደኑ በውስጡ በርካታ የሆኑ የእጽዋት ዝርያዎች, አእዋፋቶች እና ብርቅዬ የሆኑ የዱር እንስሳቶች ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህም የዱር እንስሳቶች አሳማ፣ ጉሬዛ፣ ዝንጀሮ፣ ጅብ፣ ጦጣ እና ሌሎችንም የዱር እንስሳቶች ይገኙበታል፡፡ ሌላኛው ለደኑ ትልቅ ውበት ሰጥቶት የሚገኝ የመጌቻ ወንዝ አጠገቡ ይገኛል፡፡ አምባ ደን በቀበሌው ህብረተሰብ ተጠብቆ የሚኖር ደን ነው፡፡ ደኑ ሚጠብቀው እንኳን አዋቂው, ሽማግሌው ብቻ ሳይሆን ህጻናቶችም ጭምር ልዩ ትኩረት ሰጥተውት እንደሚጠበቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ደን ውስጥ አንድ እንጨት ሲቆርጥ ቢገኝ እንኳን በቀበሌው ማህበረሰብ በባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት እንደሚቀጣ ነው፡፡ በደኑ ውስጥ በርካታ የሆኑ የዕፅዋት ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህም እድሜ ጠገብ የሆኑ የሀበሻ ጽድ, ዝግባ እና ቀርከሀዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ቀርከሀ በአሁን ወቅት እየጠፋ መምጣቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንግዲህ ውድ አንባቢያን ይህን እጅግ አስደናቂ እና የቱሪስት ቀልብ የሚስብ የተፈጥፎ ጥቅጥቅ ደን መጥታችሁ እንድትጎበኙት መልዕክታችን እናስተላልፋለን፡፡







