



አገር ልትገነባ የምትችለው በትውልድ ቅብብሎሽ መሆኑን በመገንዘብ ወጣቱ ተገቢ ያልሆኑ የሚዲያ አጠቃቃሞችን በመታገል በሀገሪቱ ሰላምና እድገት ላይ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተገለፀ ።
“ሚዲያ ለላቀ ልማት ለወረዳችን ከፍታና ለዘላቂ ሰላም የወጣቱ ሚና “በሚል መሪ ሀሳብ በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ከቀበሌ ለተወጣጡ ወጣቶች ስልጠና ተሰጥቷል ።
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪው አቶ ዘውዱ ዱላ በስልጠና መድረኩ ተገኝተው እንደተናገሩት የዚህ መድረክ ዋና አላማ በሀገር ሰላምና ግንባታ ላይ የወጣቱ ሚና ከፍ ማድረግ እንደሆነና እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ65%በላይ የወጣት ህበረተሰቡ ክፍል ሲሆን ይህም ወጣት አምራች ፡ ለቴክኖሎጂ ቅርብ ፡ ለሰላምና ኢኮኖሚ ግንባታ ዘብ የሚቆም ነው።
ሰላም ሚመጣው በዜጎች የተባበረ ተሳትፎ መሆኑን በመገንዘብ ሰላም ለማፅናት የተጀማመሩ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ወጣቱ በባለቤትነት መሳተፍ ይገባዋል ያሉት አቶ ዘውዱ ወጣቱ የአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ በመተንተን ክፍተቶችን ለይቶ በማገዝ ማህበረሰቡን ሊያማርሩ የሚችሉና የጥቂቶቹ ወይንም የግለሰብ ጉዳዮች ላልተፈለገ ቦታ ሊወስዱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ወጣቱ በማጤን የሰላም ዘብ ሊሆን ይገባልም ብለዋል።
የእዣ ወረዳ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ተሾመ ስራኒ ዛሬ ያለንባት ሀገር በብዙ መስዋዕትነት የቆየች ስትሆን በተለይም ቀደምት የነበሩ አባቶቻችን ብዙ ዋጋ ከፍለው ያቆያት እንደሆነና አሁን ያለው ትውልድ ለቀጣዩ ምን ሰርቶ ማለፍ እንዳለበት በመገንዘብ የድርሻችንን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው ዋንኛው የቀውስ ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ያለው ያልተገባ የሚዲያ አጠቃቀም ሀገራችን እንዳትረጋጋ እያደረጋት ካሉ ጉዳዮች አንዱና ዋንኛው መሆኑን በመገንዘብ ሚዲያ ለበጎ አላማና ለለውጥ መጠቀም ይገባልም ያሉት አቶ ተሾመ ለሀገር ብልጽግናና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ አበርክቶ ስላለው ወጣቱ በያለበት አካባቢ በሁሉም መስክ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።
የእዣ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ ነሪ በበኩላቸው ያለ ወጣቶች ሙሉ ተሳትፎ ሰላምንና ብልጽግናን በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደማይቻል በመገንዘብ ወጣቶች በሚዲያ አጠቃቀም ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች መሆን እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል ።
በቀጣይም ወጣቶች በተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች ሁሉ ውጤታማ በመሆን የሀገራቸውን ሰላምና ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው አቶ ፍቅሬ ተናግረዋል።
በእለቱም በወጣቱ ሚና እና በሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ በወጣቶችና ስፖርት ፅ/ቤትና በወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት በኩል ሰነድ ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።







