




የጉራጌ ብሄረሰብ ባህላዊ እሴቶቻችን እንዲጎለብቱና ለትውልድ እንዲሸጋገሩ እየተሰራው ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተገለፀ።
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ያሱራና ዋርቢያ ቀበሌ የሸራር ቤተሰብ ባካሄደው 12ኛ ዙር ንግስናና መሪ የመሾም ስነ ስርዓት ላይ ባርአዝማች ውቅያኖስ ተሰማ አንግሷል።
በፕሮግራሙ የታደሙት የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እንዳሉት የጉራጌ ማህበረሰብ ዲሞክራሲን አስቀድሞ በመለማመድ የሚታወቅ ሲሆን ምንም ማያወላዳና ግልፅ የሆነ ከጥንት ጀምሮ ዘመናዊ የፍትህ ስርዓት ሳይኖር ተበዳይ ሳይገፋ አቅም የሌለው በጉልበተኞች እንዳይደፈጠጥ መብቱ እንዲከበር የራሱ ባህላዊ ስርዓት ያበጀ ነው።
አለም የእናቶች ቀን ብሎ ሀሳብ ሳይጀምረው የጉራጌ ማህበረሰብ የእናቶች በዓል አንትሮሸት፡ የልጃገረዶች ቀን ነቐ ፡ ይፍተዝፓር ፡ የሸት ሸረትና የመሳሰሉት ለእንስሳትም ጭምር ነፃነት የሚሰጥበት የመስቀልና አረፋ በዓል ላይ በርካታ ዘመን ተሻጋሪ ባህሎችን ያስቀመጠ ነው ያሉት ሀላፊዋ ዛሬም በእዣ ወረዳ ያሱራና ዋርቢያ ቀበሌ በሸራር ቤተሰብ ያየነው የንግስናና መሪ የመምረጥ ስርዓት የሰለጠነው አለም እንኳ ብዙ የሚጋፋበትና በሰላማዊ መንገድ የስልጣን ሽግግር ከማድረግ ይልቅ አላስፈላጊ ነውጥ ውስጥ ሚገባበትን ጉዳይ እንዴት በዲሞክራሲያዊ መንገድ ስልጣንን ከአንዱ ወደ አንዱ እጅግ በሚደንቅ መንገድ ማሸጋገር እንደሚቻል ያስተማረ ነው ብለዋል ።
ፕሮግራሙም ሌሎችም ጎሳዎችና ሀይማኖቶች ሳይነጣጥል በአንድነት መንፈስ መደረጉ እጅግ የሚደንቅ በመሆኑ ይህንን እንደ ባህል ተጠብቆ እንዲኖር የመመዝገብ ስራ ለመስራት ጥረት ይደረጋልም ብለዋል።
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በበኩላቸው በሀገራችን ኢትዮጵያ በባለፉት ሰባት ዓመታት የጉራጌ ባህላዊ እሴቶቻችን እንዲጎለብቱና ለትውልድ እንዲሸጋገሩ መንግስት ጥረት አድርጓል።
ጉራጌ ከራሱ አልፎ ለሌላው የሚተርፍ ድንቅ ባህልና መተዳደሪያ ደንቦች ያለው ፡ አምራች፡ ሌላውን በፍቅር አቅፎና ተባብሮ የሚኖር ማህበረሰብ እንደሆነም ዋና አስተዳዳሪው ጨምረው ተናግረዋል።
በዛሬው እለትም የተካሄደው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየውን በእዣ ወረዳ ከሚጠቀሱ ጎሳዎች አንዱ የሆነውን የሸራር ቤተሰብ ከ800 ዓመት በፊት ጀምሮ የነበረው አዝማችነት ሴራ በያስሁራ ቀበሌ የባር አዝማች ተሰማ ፊጣ ስልጣን በልጅ ልጃቸውን ለ12ኛ ዙር የማስተላለፍ ስርዓት መደረጉን ማህበረሰባችን በስልጡን መንገድ ስልጣንን የማስተላለፍ ባህል ማሳያ ነው ያሉት አቶ ዘውዱ ስልጣኑ የተረከቡት ባርአዝማች ውቅያኖስ ተሰማ በአግባቡ ህዝቡን በመምራት ሀላፊነቱ መወጣት እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የዚህ ዝግጅት አስተባባሪ አቶ ደንድር ባባድር በበኩላቸው ዛሬ የተደረገው የወርቅ አንባር የዛሬ 800 ዓመት ጀምሮ ሲተላለፍ የመጣ ታሪካዊ ቅርስ ሲሆኑ አንባሮቹም ሁለት የወርቅና አንድ የብር በድምሩ 3 መሆናቸው ጠቅሰዋል ።
ታሪካዊ አመጣጡም በዚህ ጎሳ ቤተሰብ ከንጉስ ዋረብየ ጀምሮ ብሽንየንበር እያለ በዛሬው እለት የነገሱት ባርአዝማች ውቅያኖስ ተሰማ ድረስ የመጣ ባህላዊ ስርዓት ነው ብለዋል።
በዛሬው እለት ሀላፊነት የተሰጣቸው የዚህ ቤተሰብ አንድነት ጠብቆ የማስኬድ ፡ እንደ እዣ ብሎም እንደ ጉራጌ በሚደረጉ ውይይቶችና ልማቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ በትኩረት መስራት ይገባቸዋልም ብለዋል።
ንግስናና መሪ የመሾም ስነ – ስርዓት በተለያዩ ባህላዊ ስነ ስርዓቶች የተካሄደ ሲሆን ለአዲሱ ንጉስም የብርና የቁሳቁስ ስጦታዎች ተበርክቶላቸዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።







