የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

========================

መጋቢት18/2016ዓ.ም
የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አዘጋጅነት ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የልማት ስራ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በልማት ስራ ጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

በወረዳው 58 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በማኑፋክቸሪን፣ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው የአካባቢው ልማት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህም ከ5 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠራቸውም ባለፈ የወረዳው ገቢ በማሳደግ ከሚመደብለት በጀት 70 ከመቶ የሚሆነውን በራሱ መሸፈን መቻሉን ዋና አስተዳዳሪ ገልጸዋል፡፡

በርካታ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው የተለያዩ የመስኖ ልማቶች ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት እርባታ ተሰማርተው እራሳቸውንና የአካባቢው ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጣቸውም በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አቶ ዘውዱ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ዘውዱ ገለጻ ለሰራተኞች ምቹ የስራ አካባቢ እንዲኖር በማሰብ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው ሁለት ለቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ህንጻዎች አንዱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በዝግጅት ላይ የሚገኝ መሆኑንና የቀሪው ህንጻም ግንባታ እየተፋጠነ ይገኛል፡፡

በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ መልስ በበኩላቸው በመስክ ምልከታው በወረዳው የሚገኙ የተለያዩ የልማት ስራዎች ያሉበት ደረጃ በማየት ጥንካሬያቸውና ጉድለታቸውን በመለየት የሚመለከታው ባለድርሻ አከላት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉላቸው እና መረጃ ለህብረተሰቡ ለመስጠት እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

በልማት ስራ ጉብኝቱ በርካታ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በመስኖ የተለያዩ የልማት ስራዎች በመስራታቸው በሀገሪቱ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት፣ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠርና ልምዳቸው በማካፈል ሌሎች ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሰሩ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኙ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በመስክ ምልከታው ከታዩ ኢንቨስትመንቶች መካከል የኤማናው ትሬዲንግ አንዱ ነው፡፡ የፋብሪካው ስራአስኪያጅ አቶ አድማሱ ደገሙ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት በማድረግ የተነባበረ ጣውላ እያመረተ መሆኑንና ከ50 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡

ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራ የገለጹት አቶ አድማሱ የመብራት መቆራረጥ ችግር የሚመለከተው አካል እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡

በማህበር ተደራጅተው በመሰኖ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ጎመንና የበጋ መስኖ ስንዴ ከሚያመርቱ ወጣቶች መካከል አቶ ጌታቸው ብሩ እንደተናገረው በመስኖ ማምረት ከጀመሩ ወዲህ ከሚያገኙት ገቢ የራሳቸውና የቤተሰባቸውን ኑሮ መምራት ከመቻላቸውም ባለፈ ለሌሎች ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡

የተሻሻሉና መደበኛ ክትባት በአግባቡ በመስጠት ጤና የተጠበቀ ማህበረሰብ እንዲኖር መስራት እንደሚገባ ተገለፀ ።

===========================

የተሻሻሉና መደበኛ ክትባት በአግባቡ በመስጠት ጤና የተጠበቀ ማህበረሰብ እንዲኖር መስራት እንደሚገባ ተገለፀ ።

የእዣ ወረዳ ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተለያየ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይትና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።
የእዣ ወረዳ ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ ሰይድ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ወቅታዊ የተሻሻሉና መደበኛ ክትባቶች በተገቢው በመስጠት የህጻናት ሞት በመቀነስ እንዲሁም የማህበረሰቡ ጤና ለመጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል ።
ስልጠናው በርካታ ርዕሰ ጉዳዮቾ ላይ ያተኮረ መሆኑን የጠቀሱት ሀላፊው በቀጣይ ለ10 ተከታታይ ቀናት የሚካሄደውን ከሳንባ ነቀርሳ ታማሚ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች በመለየት ምርመራ የማድረግ ተግባር ላይ ትኩረት ያደረገ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በመድረኩ ቆይታም የተቋሙ የ8ወር አፈፃፀም ፡ ከዞንና ከክልሉ የተሰጡ ግብረ -መልሶችና በባለፈው ዓመት በአፈፃፀም ወቅት ያጋጡሙ ጉለቶች በመለየትን በአፋጣኝ ሚታረሙበትን ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገም እንደነበር አስረድተዋል።
በቀጣይም እንደ ወረዳው ለተከታታይ 10 ቀናት የሚካሄደውን ከሳንባ ቲቪ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ልየታ የማድረግና ከ15 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት ቲቢቲ መድሃኒት በጤና ባለሙያ የሚሰጥ መሆንኑ አስረድተዋል ።
በስልጠና መድረኩ ላይ የጤና ጽ/ቤት ባለሙያዎች የተለያዩ ሰነዶች አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው በቀጣይ በጤናው ዘርፍ ቀልጣፋና ወቅታዊ ክትባቶች በአግባቡ በመስጠት ህብረተሰቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በባለቤትነትና በተጠያቂነት ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሶአል።
የቀበሌ ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ፡ የጤና ጣቢያ ሀላፊዎች ፡ የጤና ጣቢያ ትስስር ባለሙያዎች እንዲሁም የፅ/ቤት ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።

በእዣ ወረዳ በሁሉም ቅድመ አንደኛ ጣቢያዎች ህፃናት የአፈ መፍቻ ቋንቋቸው በሆነው በጉራጊኛ ቋንቋ እንደሚማሩ የወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት አስታወቀ ።

==================================

በእዣ ወረዳ በሁሉም ቅድመ አንደኛ ጣቢያዎች ህፃናት የአፈ መፍቻ ቋንቋቸው በሆነው በጉራጊኛ ቋንቋ እንደሚማሩ የወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት አስታወቀ ።
ፅ/ቤቱ እንደ ወረዳው የታተመው የጉራጊኛ ቋንቋ ደረጃ አንድና ሁለት የቅድመ አንደኛ የጉራጊኛ መፅሀፍ ከጣቢያ አመቻቾች ጋር የትውቅ ፕሮግራም አካሂዷል።
የእዣ ወረዳ ም/አስተዳዳሪና የትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ እንደገለፁት የጉራጊኛ ቋንቋ በስርዓተ ትምህርት ተካቶ ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ መደረጉ ቋንቋውን ለማልማትና ለማጎልበት ጉልህ ድርሻ ከመኖሩም በተጨማሪ ህፃናት በቀላሉ ሀሳባቸው መግለፅ ያስችላቸዋልም ብለዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ከህፃናት መብቶች አንድ ህፃናቶች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር እንዳለባቸው ተቀምጧል ያሉት አቶ ተጠምቀ በመሆኑም ህፃናቶች ከወዲሁ በቋንቋቸው ፊደል በመለየት በቀጣይ እንደ ዞኑ በአንድኛ ክፍል የሚጀመረውን የጉራጊኛ ትምህርት ከወዲሁ መዘጋጀት አለባቸውም ብለዋል።
ይህም የትውውቅ ፕሮግራም ለሁለተኛ ዙር የጉራጊኛ የፊደል ልየታ ገበታ ዙሪያ የሚሰጥ ስልጠና መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው ከዚህ ቀደም በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ያሰልጣኞች ስልጠና የሰለጠኑት ለሌሎች በማሰልጠን እንዲሁም በትምህርት ቤት ደረጃ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ጣቢያ ላይ መሰልጠን እንዳለባቸው በማመን ሁሉም የቅድመ አንደኛ አመቻቾች ስልጠናውን መውሰዳቸውንም አብራርተዋል ።
” ከጋበር ” በጎ አድራጎት ድርጅት ፡ ከማህበረሰቡ እንዲሁም ከመንግስት ጋር በመቀናጀት 370 የጉራጊኛ ቋንቋ ደረጃ አንድና ሁለት የቅድመ አንደኛ መፅሀፎች መታተማቸውን የጠቆሙት አቶ ተጠምቀ ለዚህም ህትመት ከ150 ሺህ ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸዋልም ብለዋል።
እንደ ወረዳው ቅድመ አንደኛ ላይ በደረጃ አንድና ሁለት እየተሰጠ ነው ያለውን ትምህርት በቀጣይም ሁሉም ጣቢያዎች በጉራጊኛ ቋንቋ ብቻ መሰጠት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀጧል ብለዋል ።
በመሆኑም አመቻቾች ይህንኑ በመገንዘብ በቂ ግንዛቤ ይዘው ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን እንዲማሩ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በእለቱም ስለ ጉራጊኛ ቋንቋ ምንነት እና አስፈላጊነት ዙርያ በፅ/ቤቱ የጉራጊኛ ቋንቋ አስልጣኝ ባለሙያዎች በአቶ ሳህሉ በረዳ እና በመምህርት ወ/ሮ ጥርርወርቅ ንጋኒ ማስገንዘቢያ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል ።
በእለቱም ከወረዳው ት/ቤቶች የተውጣጡ ርዕሳነ-መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና የጽ/ቤት ባለሙያዎች ተሳታፊ ነበሩ ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው፡፡

 

የወልቂጤ ከተማ እግር ካስ ክለብ በፋይናንስ ለማጠናከር በተከናወነው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ተገለፀ ።

*========================*

የወልቂጤ ከተማ እግር ካስ ክለብ በፋይናንስ ለማጠናከር በተከናወነው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ተገለፀ ።
የወልቂጤ ከተማ እግር ካስ ክለብ የገቢ ማሰባሰብያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ተካሄደ።
ክለቡ በፋይናንስ ለማጠናከር በተከናወነው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ተገልጿል።
በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው እንደገለጹት ስፖርት ለሰላም ለፍቅር ለጤና ለአንድነት ጉልህ ድርሻ አለው።
በስፖርቱ ዘርፍ በትኩረት በመስራት ለሀገር ማበርከት እንደሚያስፈልግ ገልጸው የወልቂጤ ከተማ እግር ካስ ክለብ የማህበረሰቡን አንድነት ፣ባህልና ታሪክ በመጠበቅ በገጽታ ግንባታ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል።
ቡድኑ ስለ ልምምድና ስለመጫወት ብቻ ማሰብ አለበት ያሉት አቶ እንዳሻው ክለቡ የሁሉም አምባሳደር በመሆኑ ሁሉም ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል።
ደመወዝ ሳይከፈል መጫወት አይቻልምና በስፖርቱ ዘርፍ ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው በስፖርቱ ዘርፍ በዞኑ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው የወልቂጤ ከተማ እግር ካስ ክለብ በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን የገንዘብና ሌሎች ድጋፎች ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው እንደገለጹት ከተማው በእግር ካስና በቅርጫት ካስ በፕሪምየር ሊግ በመሳተፍ ላይ ነው።
በተለያዩ ችግሮች ውስጥም ሆኖ ክለቡ የጉራጌ ባህል ፣ታሪክና እሴት ጎልቶ እንዲወጣ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ክለቡ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው እየተሰራ ነው ያሉት አቶ እንዳለ ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ክለቡ በፋይናንስ ለማጠናከር በስካይ ላይት ሆቴል በተከናወነው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ተገልጿል።
በገቢ ማሰባሰቢያ መረሃግብሩ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ እንዳሸው ጣሰው፣የዞንና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል።

የአገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተጨማሪ የሚያስፈልጉት የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሟሉ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ ።

*=======================================*

የአገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተጨማሪ የሚያስፈልጉት የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሟሉ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ ።
በሆስፒታሉ በ2016 በጀት ዓመት 6 ወራት የተከናወኑ ተግባራቶች የቦርድ አባላት ገምግሟል ።
የአገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የቦርድ ሰብሳቢና የጉራጌ ዞን ብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ ወ/ሮ አመተሩ ኡፍ ሁሴን እንደገለፁት የአገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለማህበረሰቡ ያለው ፋይዳ በመረዳት ተገቢው አገልግሎት እንዲሰጥ በጉለት የተጠቀሱ የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሟሉ ሁሉም የድርሻው መወጣት ይገባል ።
በሆስፒታሉ የገጠሙ ችግሮችን በመለየት የሚፈቱበት መንገድ ላይ ሰፊ እንቅስቃሴዎች መደረጉ የሚበረታታ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ አሁንም ያልተፈቱ ችግሮችን ከዚህ በተሻለ መልኩ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቃልም ብለዋል።
የተገለፁትም የግብዓት ችግሮች ለመቅረፍ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት መዋቅሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሰፊ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ወ/ሮ አመተሩፍ አስገንዝበዋል ።
የእዣ ወረዳ ም/ አስተዳዳሪና የትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ በበኩላቸው ሆስፒታሉ እንደ ወረዳው መንግስት ከበጀት ድጋፍ ጀምሮ የሰው ሃይል በመቅጠር አገልግሎት እንዲሰጥ በተቻለ አቅም የተለያዩ ስራዎች እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል ።
በቀጣይም ሆስፒታሉ የገጠመው የህክምና ቁሳቁስና ሌሎችም ችግሮች ለመቅረፍ አሁንም ከመንግስት የሚጠበቁ ስራዎችና ድጋፎች በማድረግ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ በተቻለ አቅም እንደሚሰራም አቶ ተጠምቀ ገልፀዋል።
የአገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ ስኪያጅ አቶ ጥላሁን ሀይሌ የ2016 በጀት ዓመት የ6 ወር ስራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ማህበረሰቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሆስፒታሉ አገልግሎት እየተረዳ በመምጣቱ ተጠቃሚውን ማህበረሰብ እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሆስፒታሉ ባለው የሰው ሀይል የተሟላ አገልግሎት እንዳይሰጥ የጨቅላ ህፃናት የህክምና ቁሳቁስ ፡ የኤክስሬ ማሽን ፡ የቀዶ ጥገና አገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች የሰው ሃይል እጥረትና ሌሎችም ባለመሟላታቸው በሆስፒታሉ ደረጃ መስጠት ሚገባ የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ባለመሆኑ ሁሉም በየደረጃው ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል ።
የቦርድ አባላቶችም በሰጡት አስተያየትም ሆስፒታሉ በዚህ ዓመት ባለው የሰው ሃይልና የህክምና ቁሳቁስ ለማህበረሰቡ እየሰጠው ያለው አገልግሎት ከሌላ ጊዜ መሻሻል የታየበት መሆኑን አመላክተው በቀጣይም ከዚህ በተሻለ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ የግብዓቶና ሌሎችም የተለዩ ችግሮች እንዲፈቱ ሁሉም ሀላፊነቱ መወጣት እንደሚገባውም ተናግረዋል።
በእለቱም የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ አየለ ፈቀደ ፡ የእዣ ወረዳ ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ ሰይድ ጨምሮ ሌሎችም የቦርድ አባላት በውይይቱ የተገኙ ሲሆን የቦርድ አባላቱም በሆስፒታሉ አጥር ግቢ በውጤታማነት የሚገለፀው የ30- 40-30 የፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክትና የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።

የመምህራን ስልጠና በይፋ ስለመጀመሩ:

*=============================*

የመምህራን ስልጠና በይፋ ስለመጀመሩ:

የካቲት 11-16 ድረስ ጋበር ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተመረጡ የት/ርት ዘርፎች ላይ በአጠቃላይ ለ153 የመካከለኛና ከ/2//ደረጃ ት/ቤቶች መምህራን የሚሰጠው የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በይፋ  ተጀምሯል። በመክፈቻውም የዩኒቨርሲቲው ተወካዮች ረ/ፕ አበበ ያበኬር (Industry linkage Director) እና ረ/ፕ ቸርነት ዘርጋ (Director for Community Service) እንዲሁም የኧዣ ወረዳ መስተዳድር፣ የት/ት ፅ/ቤትና የጋበር ሥራ አስኪያጅ በተገኙበት መምህራን ስልጠናውን በከፍተኛ ትኩረትና ጥብቅ ሥነ-ሥርአት ይከታተሉ ዘንድ በማሳሰብ በይፋ እንዲጀመር አድርገዋል። ሰልጣኝ መምህራንም የሚወስዱት ስልጠና ውጤት የሚታየው ተማሪዎቻቸው ላይ እንደሆነ የመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ ከአደራ ጭምር ተነግሯቸዋል ከዚህም በተጨማሪም አሁን ከሚሰለጥኑት መካከል ተመርጠው ወደፊት አቅም በፈቀደ መጠን ከ1-6 ክፍል ለሚያስተምሩ መምህራን ከጋበር ጋር በመተባበር የሸመቱትን እውቀት እንዲያወርዱት ጥረት እንደሚደረግም ተገልፆላቸዋል። በዚህ አጋጣሚ ስልጠናው የሚሰጥበትን ክፍሎችና ቁሳቁሶች ለአስልጣኞች የመጠጥ ውሐ ጭምር በማቅረብ ታላቅ ትብብር ያደረገልንን የአገና ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ኮሌጅን እጅግ አድርገን እናመሰግናለን!!

ጋበር የበጎ/አ/ድ

ከሚያራርቁ የሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት አንድነትና ሰላማችን ማስከበር እንደሚገባን ተገለፀ ።

**************************************

ከሚያራርቁ የሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት አንድነትና ሰላማችን ማስከበር እንደሚገባን ተገለፀ ።

የእዣ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ፅ/ቤት በሀይማኖትና እምነት ጉዳዮች ለቀበሌ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላትና ለሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ስልጠና ሰጥቷል ።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ከቀድሞ ጀምሮ የነበሩትን የመከባበር ፡ የመቻቻልና የአንድነት እሴቶች ሰላም በማይፈልጉ አንዳንድ ሀይሎች እንዳይደበዝዙ በንቃት መሰራት ይገባል ።

ከሚያራርቁ የሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት አንድነትና ሰላማችን ማስከበር እንደሚገባን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ለዚህም የሀይማኖት አባቶች ሃላፊነታቸው እጥፍ ድርብ መሆኑን በመገንዘብ አልፎ አልፎ በወረዳው የሚስተዋሉ የፅንፈኝነት እና የአክራሪነት እንዲሁም የተዛቡ አስተሳሰቦች ለማረም የጎላ ሚና መጫወት ይገባቸዋልም ብለዋል ።

ትብብርን ሳይሆን ፉክክክርን ማዕከል የሚያደርጉ ጉዳዮች መታረም አለባቸው ያሉት አቶ ዘውዱ በአንዳንድ ቤተ እምነት በሚስተዋሉ የአስተምሮ ችግሮች በፅኑ በመታገልና በማውገዝ የተጀመረውን የሰላም ሁኔታ እንዲዘልቅና እንዲፀና የሀይማኖት አባቶች ከመንግስት ጋር በመተባበር የበኩላችንን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የእዣ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ፅ/ቤት ሀላፊ ደመቀ ሀብቴ በበኩላቸው የሀይማኖት ተቋማት ትውልድን በመቅረፅ ረገድ ትልቅ ሚና ያላቸው ሲሆን በዚህም የተገነባ ትውልድ ለወረዳው ብሎም ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

በወረዳው ለረጅም ጊዜ የቆየውን የማህበረሰቡ ሰላምና አንድነት በላቀ መልኩ እንዲቀጥል ርብርብ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው ያሉት አቶ ደመቀ በወረዳ አንዳንድ ጥቂት የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ከጥንት ጀምሮ የቆየውን የማህበረሰቡ አንድነትና ሰላም እንዳያዛቡ በተረጋጋ ሁኔታና በጥልቀት በመገንዘብ የሀይማኖት አባቶች ያላቸውን ትልቅ አደራና ሀላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል ።

የፅ/ቤቱ ባለሙያ የሆኑት አቶ ቶፊቅ ሺፋ በወረዳው በሀይማኖትና እምነት ላይ ትኩረት ያደረገ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን የእምነት ተቋማት ከየትኛውም ፖለቲካ ሰለባ እንዳይሆኑ ነቅቶ በመጠበቅ የራሳቸውን አስተምሮት ብቻ ላይ በማተኮር ለወረዳው ብሎም ለሀገር ሰላምና ለህዝቡ አንድነት እንዲሁም መፈቃቀር ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠንክረው መስራት እንዳለባቸውም በሰነዱ አመላክተዋል ።

በእለቱም የተሳተፉት የሀይማኖት አባቶች በሰጡት አስተያየትም በየቤተ እምነቱ ያሉት የሀይማኖት አባቶች አንዳንድ ችግሮች ሲኖሩ መግባባት እንዲፈጠር የተጣለባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎች አክለውም በተለይም የሀይማኖት አባቶች በየቤተ እምነታቸው ለምዕመናኑ በሰላምና በአብሮነት ላይ አስተምሮት ላይ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል ።

በቀጣይም ለወረዳው ብሎም ለሀገር ፍፁም ሰላምና አብሮነት ላይ በመንግስት ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የሀይማኖት አባቶች የድርሻቸው እንደሚወጡም በአስተያየታቸው ተናግረዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው ።

በቦዠባር ከተማ አዲስ መናኸሪ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ፅ/ቤት አስታወቀ ።

****************************

በቦዠባር ከተማ አዲስ መናኸሪ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ፅ/ቤት አስታወቀ ።
መናኸሪያው ተገንብቶ አገልግሎት መጀመሩን ለተለያዩ እንግልት ከሚዳርጉና ያለአግባብ ወጪዎች የሚቀርፍ እንደሆነም በከተማው ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል ።
የእዣ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም አወል የአገልግሎቱ አሰጣጥ በተመለከቱበት ወቅት እንደገለፁት በከተማው የሚሰጠውን የትራንስፖርት አገልግሎት ህጋዊ ለማድረግ የመናኸሪያው መገንባት ፋይዳው የጎላ ነው ።
ቦዠባር ከተማ ለማደግ ብዙ ምቹ ሁኔታዎችና እድሎች አሉት ያሉት ሀላፊው ከነዚህም መካከል አንዱ ከፍተኛ የምርት አካባቢ በመሆኑ ብዙ የትራንስፖርት ፍሰት አለው ብለዋል ።
በመኑም በከተማው ህገ -ወጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለአብነትም ከታሪፍ በላይ ማስከፈል ፡ ትርፍ ጭነት ፡ በፈለጉት አካባቢ መስራት እንዲሁም ማህበረሰቡ በዘርፉ ማግኘት ያለበትን አገልግሎት ያለማግኘት ችግሮች ተጠቃሽ እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ኢብራሂም ይህንን የመናኸሪያ አገልግሎት መጀመሩን እነዚህ ክፍተቶች ቀስበቀስ ለመቅረፍ የሚቻልበት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
ይህንን ተቋም ስራ ለማስጀመር ምንም እንኳ ካሳ ተከፍሎአቸው ቢሆንም የይዞታ ባለቤት ከሆነው አርሶአደር ጀምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ትብብር አድርገዋል ያሉት ሀላፊው በተለይም የወረዳው መንግስት ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት እስከሚጀምርበት ሰዓት ድረስ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል አድርጎአልም ብለዋል።
በአጠቃላይ ለዚህ መናኸሪያ ለባለይዞታዎች ካሳ ከመክፈል ጨምሮ እስከ ሙሉ ግንባታው ከ5ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም አቶ ኢብራሂም አክለው ገልፀዋል ።
በቀጣይ የሚፈልገውን ጤናማ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር የማህበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል ያሉት ሀላፊው ህብረተሰቡም በመናኸሪያው ውስጥ በመሳፈር ፡ ትርፍ ባለመጫንና ከታሪፍ በላይ እንዳይከፍል ከተቋሙ ብሎም ከመንገድ ደህንነት ባለሙያዎች ጋር ተናቦ መስራት እንደሚገባውም መልዕክት አስተላልፈዋል ።
የቦዠባር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራስኪያጅ አቶ ሲሳይ ሽምሳ በበኩላቸው በከተማው ከተሰሩ ዋና ዋና ተግባራት አንዱ ይህ የመናኸሪያ ግንባታ ሲሆን ይህም አገልግሎት እንዲጀምር ከፍተኛ ገንዘብና ሰፊ እርብርብ ተደርጎበታል ብለዋል ።
ይሆም እንዲሳካ የወረዳው መንግስት ከገንዘብ ድጋፍ አንስቶ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጎአል ያሉት አቶ ሲሳይ የቦዠባር ማህበረሰብም የመናኸሪያ ቦታ ግንባታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በተለያየ መልኩ ተሳትፎ ማድረጉንም ጨምረው ተናግረዋል።
በቀጣይም መናኸሪያው ለማህበረሰቡ አስፈላጊውን ጥቅም እንዲሰጥ ከወረዳው ሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትጋት ይሰራል ያሉት አቶ ሲሳይ ህብረተሰቡም መናኸሪያው ያለው ከፍተኛ ጥቅም በመገንዘብ ከመናኸሪያ ውጪ ባለመሳፈርና ህገወጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሲኖር ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት አገልግሎቱ በተፈለገው መንገድ እንዲሰጥ የድርሻውን መጫወት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በከተማው ያነጋገርናቸው አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎችም መናኸሪያው ተገንብቶ አገልግሎት መጀመሩ ለተለያየ ችግር ከሚዳርጉ እንግልትና ያላግባብ ወጪዎች የሚቀርፍ ነው ብለዋል።
በከተማው ከዚህ በፊት የትራንስፖቱ አገልግሎቱ የነበረው በአስፋልት ዳር መሆኑን ተከትሎ ለትራፊክ አደጋ ከፍተኛ ስጋት ነበር ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ መናኸሪያ መገንባቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት በመሆኑ ለዚህም ስኬት የወረዳው መንግስትና ለከተማ ማዘጋጃ ቤቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው ።

የመላው እዣ ወረዳ የልዩ ልዩ ስፖርቶች ሻምፒዬና ከዛሬ ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገለጸ ።

*=============================*

የመላው እዣ ወረዳ የልዩ ልዩ ስፖርቶች ሻምፒዬና ከዛሬ ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገለጸ ።
የእዣ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት የወረደው የልዩ ልዩ ስፖርቶች ሻምፒዬና ከቀን 13/06/2016 አ/ም ጀምሮ ሁሉንም የወረዳው ት/ቤቶችንና ቀበሌዎች ባማከለ መልኩ የተለያዩ የስፖርት ውድድሮች የሚካሄድ መሆኑን ጽ/ቤቱ ገልፆአል ።
ፅ/ቤቱ ይህንን ውድድር ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆን ከሚመለከተው አካላት ጋር በትላንትናዉ እለት ውይይት መድረጉንና አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ከፅ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።
በዚህም ውድድር ወረዳውን ወክለው የሚሳተፋ ምርጥ ስፖረተኞችን በመምርጥ በዞን ለሚደረገው የልዩ ልዩ ስፖርትና ባህል ስፖርት ውድድር ተሳታፊ እደሚሆኑ ተገልጾል።

ተቋማት በእቅድ ላይ የተመሰረት አገልግሎት በመስጠትና ቀልጣፋነትና ውጤታማነት በማረጋገጥ ህብረተሰቡን ማገልገል እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ፅ/ቤት አስታወቀ ።

*******************************

ተቋማት በእቅድ ላይ የተመሰረት አገልግሎት በመስጠትና ቀልጣፋነትና ውጤታማነት በማረጋገጥ ህብረተሰቡን ማገልገል እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ፅ/ቤት አስታወቀ ።
ፅ/ቤቱ ለቀበሌ ስራስኪያጆች በተቀናጀ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ እና በተገልጋይ ዳሰሳ ጥናት ላይ ስልጠና ሰጥቷል።
የእዣ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ በለጠ ሳህሌ እንደገለፁት በገጠር ቀበሌዎች ደረጃ ያለውን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ ፡ ውጤታማ ፡ ፍትሀና በተቀናጀ መልኩ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ስራ በመስራት ቀጣይነት ያለው አፈፃፀም ማሻሻል ያስፈልጋል ።
አገልግሎት አሰጣጣችን በማዳበር የመልካም አስተዳደር መርሆችን ከግድግዳ ወደ ተግባር መቀየር ይገባል ያሉት ሀላፊው በቀበሌም ሆነ በተቋም ደረጃ የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶኝ በተሻለ መልኩ ማሳካት ይገባልም ብለዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በተለይም በቀበሌ ደረጃ ሚስተዋሉ ክፍተቶችና ችግሮችን በመቅረፍ ወደ ተሻለ የአገልግሎት ስርአት ለማስገባት የስራስኪያጆች ሚና የጎላ ነው ያሉት አቶ በለጠ በቀጣይም ተቋሙ የአፈፃፀም ሂደቶች ክትትሉን በማዳበር ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት የሚሰራ ይሆናልም ብለዋል።
ስራስኪያጆች ከእውሸት ሪፖርት/መረጃ/ ነፃ በመሆን ትክክለኛ መረጃ ለሚመለከተው አካል በመስጠት ዘላቂነት ያለው መፍትሄና እድገት እንዲመጣ በማድረግ ማህበረሰቡን ማገልገል እኖደሚገባም ሀላፊው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የፅ/ቤቱ ምክትል ሀላፊ አቶ ሙህዲን ሁሴን በበኩላቸው ተቋማት በእቅድ ላይ የተመሰረት አገልግሎት በመስጠትና ቀልጣፋነትና ውጤታማነት በማረጋገጥ ህብረተሰቡን ማገልገል እንደሚገባ ገልፀዋል።
በታችኛው መዋቅር ያለው አገልጋይ ወቅታዊ ሁኔታ በመረዳት በተሰማራበት የስራ መስክ የተሰጠውን ተልዕኮ በመፈፀም የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይገባዋል ያሉት አቶ ሙዲን ከምንም በላይ ሳይማር ላስተማረው ማህበረሰብ በቅንነትና የአገልጋይነት ስሜት በመላበስ ውጤታማ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል ።
በእለቱም በፅ/ቤቱ ባለሙያ በአቶ ኑርሀሰን መኑር የገጠር ቀበሌዎች ሴክተር ተኮር ሪፎርም ፡ የስራስኪያጆች ተግባርና ሀላፊነት ፡ የተቀናጀ እቅድ ዝግጅት ትግበራና ምዘና እንዲሁም በቀበሌ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የቅሬታ አፈታት ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገ የስልጠና ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል ።
ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየትም ስልጠናው እጅግ ወሳኝና በየቀበሌአቸው አገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ ወርደን ተግባራዊ እናደርጋለን ብለዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።