ለተጎጆዎች ትልቅ እፎይታ

====መንግስትና ማህበረሰቡ በመቀናጀት በተለያዩ ጊዜዎች ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ ለተጎጆዎች ትልቅ እፎይታን እየሰጠ እንደሚገኝ ተገለፀ።

ቀን 17/06/2018

ማህበረሰቡና የእዣ ወረዳ መንግስት የሚደግፈውን ድጋፍ በጋራ በማድረግ ለ7 አርሶአደሮች የ400 ቆርቆሮና 21 ፓኬጅ ሚስማር በአጠቃላይ 424,350 ወጪ በማድረግ ለተጎጂ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።

የእዣ ወረዳ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ተሾመ ስራኒ እንዳሉት እንደ ሃገር በተለያዩ አገጣሚዎች እና በተለያዩ ቦታዎች አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ገልጸው አደጋዎቹም ማህበረሰባችንን ሊጎዱ እንደሚችሉ አብራርተው መንግስት አደጋው ማህበረሰቡን እንዳይጎዳ ህብረተሰቡን በማስተባበርና መንግስት የሚደግፈውን ድጋፍ በጋራ በማድረግ ተጎጆዎችን እያገዘ እንዳለ ገልፀዋል።

እንደ ወረዳችንም እስከ አንድ ሚሊዮን ብር በመመደብ የቤት አደጋ ለደረሰባቸዉ እንዲሁም ምንም ቤት ለሌላቸውና ለሌሎች መሰረታዊ ችግሮች ጭምር ተጎጂ ወገኖችን እየደጎመ እንዳለ ገልጸው ለአደጋ ስጋት ማህበረሰቡ በራሱ የሚያዋጣው መዋጮ እንዳለም ጭምር በመግለጽ።

ተጎጂዎችንም ጨምሮ ሌሎች የማህበረሰባችን ክፍሎች ከተረጅነት በመላቀቅ አምራችነታቸውን በማረጋገጥ ምርትን በማሳደግና የራሳቸውን መሬት፤ የራሳቸውን ጉልበት፤ የራሳቸውን ሀብት በመጠቀም የተሟላ ኑሮ ለመኖር ሁሉም ባለድርሻ ካላት ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

በእዣ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የአደጋ ስጋት ዝግጅትና ምላሽ ሀላፊ አቶ ተካ ወርቁ በበኩላቸው በዛሬዉ እለትም ለ7 አባወራዎች 400 ቆርቆሮ ድጋፍ መደረጉንና ለእያንዳንዳቸው ሶስት ሶስት ፓኬጅ ሚስማር ድጋፍ መደረጉንና ለዚህም 424,350 ብር ወጪ መደረጉን በመግለፅ በተለያዩ አጋጣሚዎች አደጋ ለደረሰባቸው ወገኖቻችንን በቀጣይነት ይህንኑ ድጋፍ እንደሚቀጥል ገልፀው ።

ህብረተሰቡ አደጋ ሊያመጡአቸው የሚችሉትን ቀውሶች ቀድሞ በመረዳት ራሳቸውም ከአደጋ ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባና ሁሉም ባለድርሻ በሚፈጠሩ መድረኮች ሁሉ የግንዛቤ መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚገባ አስገንዝዋል።

ተጎጂዎቹም ለተደረገላቸው ድጋፍ የእዣን ማህበረሰብና መንግስትን አመስግነው እነሱም በተደረገላቸው ድጋፍ በቶሎ ቤታቸውን በመገንባት እና ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንደሚገቡ ገልጸዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ነው።

በተናጥል ከመስራት ይልቅ በልማት ህብረት በመስራታቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዳደረጋቸው በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ሞዴል ልማት ህብረት አባላት ተናገሩ።

በተናጥል ከመስራት ይልቅ በልማት ህብረት በመስራታቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዳደረጋቸው በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ሞዴል ልማት ህብረት አባላት ተናገሩ።

የካቲት 17/2018 ዓም

BBBC እዣ የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት በወረዳው ያሱሁራና ዋርቢያ ቀበሌ የዋርቢያ ሴቶች ልማት ህብረት እና በመንጠር ቀበሌ ይሰፋጣጥ የሞዴል የልማት ህብብረት የስራ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ያደረገ የልምድ ልውጥ አካሂዷል ።

በጉብኝቱ ወቅትም የእዣ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ አሰለፈች ክብሩ እንዳሉት ሴቶች በሀገር ደረጃ ትልቅ ተሞክሮ ጭምር እየተቀመረበት ያለው ተደራጅተው በመስራታቸው ፡ በመቆጠባቸው እና ድምፃቸው በማሰማታቸው ተጠቃሚ መሆናቸው ሲሆን እንዲሁም ሴቶች በአንድ ሲሆኑና ሲቀናጁ ፡ ማህበር ሲፈጥሩ ትልቅ አቅም ይፈጥራሉ ብለዋል ።

ለአብነት እንደ ዞኑ ተደራጅተው ሰርተው ለማዕከላዊ ክልል ጭምር ምርጥ ዘር አቅራቢ የሆኑ ሴቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ሀላፊዋ እንደ እዣ ወረዳም ሴቶች በሚገባ ከተደገፉ የዚሁ እድል ተጠቃሚ መሆን የሚችሉና ትልቅ አቅም ያላቸው በመሆናቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በደንብ መደገፍና መከታተል ያስፈልጋልም ብለዋል።

እንደ እዣ ወረዳ የሴቶች ሁለንተናዊ አቅም ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት BBBC እዣ እዣ የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት ከወረዳው መንግስት ጋር በመቀናጀት በርካታ ስራዎች እየሰራ ይገኛል ያሉት ወ/ሮ አሰለፈች በተለይም የሴቶች አቅም በማጎልበት ፡ የህፃናትና እናቶች እንክብካቤ በትምህርትና በሌሎችም የማልማት እቅድ በማዘጋጀት አበረታች ስራዎች በመስራት ላይ ይገኛልም ብለዋል ።

ድርጅቱ በዛሬው እለትም ያደረገው የሞዴል ልማት ህብረት ልምድ ልውውጥ እናቶች በአአካባቢያቸውና በአደረጃጀታቸው ትልቅ አቅም እንዲኖራቸው እድል የሚፈጥር በመሆኑ ላደረገው አርያነት ያለው ተግባር በወረዳው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በአጠቃላይ እንደ ወረዳው ሴቶች ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ባለፈ በአደረጃጀታቸው ከፍተኛ የጤና ችግር ለገጠማት እናት በከፍተኛ የህክምና ደረጃ ለማሳከም እንቅስቃሴ የሚደርጉ ቀበሌዎች መኖራቸውንም ጨምረው የገለፁት ሀላፊዋ በቀጣይም ተደራጅተው ለሚያመርቷቸው ምርቶች የገበያ ትስስር ከመፍጠር አኳያ ያሉትን ጉለቶች በማረም ይበልጥ አቅማቸው ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የBBBC እዣ የተቀናጀ የልማት ፕሮግራም ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ፍቃዱ ተስፋዬ እንዳሉት ድርጅቱ እዣ ወረዳ ከገባ 3 ዓመት ጀምሮ በዋናነት በአራት ዘርፎች ማለት በትምህርት ፡ በጤና ፡ በግብርናና ዋሽ ፕሮግራም ላይ እየሰራ ሲሆን በዚህም የባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ፡ የድሃ ድሃ ተማሪዎች ደብተርና ስክሪብ ድጋፍ ፡ በትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ፡ በጤናው ዘርፍ የእርጉዝ እናቶች ማረፊያና ሌሎችም በርካታ ስራዎች እያከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።

ድርጅቱ ከሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራቶች መካከል በዛሬው እለትም ሴቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተለይም በግብርናው ዘርፍ እንዲበቁ ይህ የልምድ ልውውጥ መደረጉን አስተባባሪው ጨምረው ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም እናቶች በግል እየሰሩ ከሚደክሙ ይልቅ በቡድን ተደራጅተው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ይህንን ሞዴል የሆኑ የልማት ህብረቶች እንዲጎበኙ መደረጉን የተናገሩት አቶ ፍቅዱ በቀጣይም በሌሎች የተደራጁ ሴቶች ከዚህ ልምድ ወስደው ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆኑም ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በልምድ ልውውጡም በወረዳው በግብርናው ዘርፍ ተጠቃሚ የሆኑ የዋርቢያ ሞዴል ልማት ህብረት እና በቃጫ ምርት እደጥበብ ስራ ጠንከራ የሆነው መንጠር ቀበሌ የይሰፋጣጥ ልማት ህብረት የስራ እንቅስቃሴ ተጎብኝቷል።

በልምድ ልውጡ የተሳተፉት እናቶችም እንዳሉ ይህ ልምድ ልውጥ ማድረጋቸ በተናጥል ከመስራት ይልቅ በልማት ህብረት በመስራታቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዳደሚያደርግ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም በየአደረጃጀታቸው ይበልጥ ጠንካራ ስራ ለመስራ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ጠቅሰው BBBC ድርጅትም በቅርበት ሆኖ በየጊዜ የሚያደርግላቸው በተለያየ መልኩ የሚገለፅ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።

ጉራጌ ዞን 5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ

====የቴክኖሎጂ ክህሎትን ለወጣቶች ለማቅረብ፣ የፕሮግራሚንግ እውቀቶች ለማስፋፋትና በዲጂታል አለም ተወዳዳሪ ለመሆን ኢቲዮ ኮደርስ ጉልህ ሚና እንዳለው ተገለጸ።

የካቲት 17/2018(ወልቂጤ)

በጉራጌ ዞን 5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ አፈጻጸም ሲትሪንግ ኮሚቴ ግምገማና የ2018 ዓ.ም የ2ኛ ደረጃ ትምህት ቤቶች የበየነ መረብ ፈተና ቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

ወጣቱ ትውልድ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያስችለውና የዲጂታል ክህሎት እንዲኖረው አላማ ያደረገ ፕሮግራም ነው።

የቴክኖሎጂ ክህሎትን ለወጣቶች ለማቅረብ፣ የፕሮግራሚንግ እውቀቶች ለማስፋፋት እና በዲጂታል አለም ተወዳዳሪ ለመሆን ኢቲዮኮደርስ ጉልህ ሚና እንዳለው በመድረኩ ተገልጿል።

በዞናችን ከ56 ሺ በላይ ሰልጣኞች በተለያዩ ኮርሶች ተምረው ኢንተርናሽናል ሰርተፍኬት መያዛቸው ታውቋል።

በዚህም በተለይም ተማሪዎች የኮዲንግ ስራ በመጀመር ድህረ ገጾች፣ ሲስተሞችና ሞባይል አፖች ማልማት መቻላቸው ተገልጿል።

በመድረኩም የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ ፣የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ፣የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማሪያም ፣የመምሪያ ኃላፊዎች፣ምክትል አስተዳዳሪዎችና ከንቲባዎች፣የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፣የትምህርት፣የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ፅ/ቤቱ የ2018 ዓም የ6 ወር አፈፃፀም ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል ።

የትምህርትን ስራ ዘወትር በመደገፍ ፡በመምራትና ወደ ተሻለ ደረጃ በማሻገር በዘርፉ ውጤታማ ስራ ማምጣት እንደሚያስፈልግ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት ገለፀ ።

የካቲት 16/2018 ዓም

ፅ/ቤቱ የ2018 ዓም የ6 ወር አፈፃፀም ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል ።

የእዣ ወረዳ ም/አስተዳዳሪና የትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ የትምህርትን ስራ ዘወትር በመደገፍ ፡ በመምራትና ወደ ተሻለ ደረጃ በማሻገር በዘርፉ ውጤታማ ስራ ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ እዣ ወረዳ በትምህርቱ ዘርፍ ውጤት እንዲመዘገብ ተደጋጋሚ መድረኮች በማዘጋጀት በተፈጠሩ ግንዛቤ መሰረት ትምህርት ቤቶች እራሳቸው እንዲመለከቱ ለማስቻልና ጉድለታቸውም በዛው ልክ እንዲያርሙ ሰፊ ሰራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው ያለንን የውስጥን አቅም በመጠቀም ፡ ባለድርሻን በማሳተፍ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሙቹ እንዲሆኑ በማድረግና የተሻለ የተማሪዎች ውጤት እንዲመዘገብ በትኩረት መስራት ያለባቸው ተቋማት አሁንም መኖራቸውንም አመላክተዋል።

በቀጣይ የስራ ግዜ የተቋም ግንባታ ፡ የሀብት አጠቃቀም ፡ የህብረተሰብ ተሳትፎ ፡ ተማሪን ማብቃት በተመለከተ ፡ 6ቱ ኢንሼቲቮች ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር እና በሌሎችም ጉዳዮች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶዋቸው እንዲመሩ አቶ ተጠምቀ አሳስበዋል።

በትምህርት ዘመኑ በእስካሁን ሂደት የተሻለ ሥራዎችን በማስቀጠል ፡ በአፈፃፀሙ የተመዘገቡ ውስንነቶችን በመቅረፍ በቀጣይ የተሻለ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ሀላፊው በተለይም የት/ቤት አመራሮችምና መምህራን ክህሎታቸውን በማሳደግ በተማሪዎች ውጤትና ስነ-ምግባር ላይ ለውጥ ለማምጣት መትጋት ይገባቸዋል ብለዋል።

የእዣ ወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ አስቻለው ወልዴ በበኩላቸው እንደተናገሩት የትኛውም መምህር የተሻለ የትምህርት አሰጣጥ ለመስጠት ራሱን ማብቃት እንዲሁም ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት እና ሁሉ ርዕሰ መምህሩም ከእቅድ ጀምሮ ሰፊ ስራዎች ለመስራት ሁሌም ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል ብለዋል።

መምህራኖቻችን ምን እንደሚመስሉ ለይቶ በማወቅ ፡ በተማሪ ውጤትና ስነ ምግባር ላይ ያላቸው አስተዋፅኦ በመለየት የመማር ማስመሩ ሂደት መፈተሽ ከርዕሰ መምህራን እንደሚጠበቅም የተናገሩት ምክትል ሀላፊው ከዚህ በተጨማሪም የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥና መቅረት ክትትል በማድረግ የመምህራን መውጫና መግቢያ ሰአት በማስተዳደር ፡ የተማሪ ስነምግባር ላይ ዘወትር ክትትል በማድረግ የትምህርት ብክነት እንዳያጋጥም መስራት እንደሚያስፈልግ አያይዘው አንስተዋል።

በቀጣይም የፈተና አሰጣጥ ዘይቤያችን ምን እንደሚመስል በሚገባ በመፈተሽ ተማሪዎችን ሊያበቃና ሊያጠነክር በሚችል መልኩ ቀርፅፆ ማዘጋጀት እንደሚገባም አቶ አስቻለው ተናግረዋል።

ተሳታፊዎቹም በሰጡት አስተያየትም እንደ ወረዳው በትምህርት ዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ስራዎችን በማስቀጠልና በአፈፃፀም ወቅት የገጠሙ ጉለቶችን ቶሎ በማረም የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል በጊዜ የለም መንፈስ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።

በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት አዘጋጅነት ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ።

ማህበራዊ ቀውሶችን በማጥፋት ጠንካራ የስራ-ባህልን በማዳበር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማምጣት ማህበረሰቡ እና በየደረጃው ያለ ባለድርሻ አካል የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ተገለፀ።

የካቲት 16/06/2018

በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት አዘጋጅነት ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ።

የእዣ ወረዳ ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም አወል እንዳሉት በየደረጃው ያሉት የመንግስት መዋቅሮች ከበጀት አመቱ ጀምሮ ስራዎችን እየሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው በዘላቂነት ችግሮችን በማውጣት መፍትሄ በመፈለግና ውይይቶችን በማዳበር የሚከሰቱ የተለያዩ ቀውሶችን ማስወገድ እንደሚገባ አብራርተዋል።

ባለድርሻ አካላትም ማህበረሰብን እንደሚመራ አካል ሽማግሌዎችና በየደረጃው ያሉ የማህበረሰብ ክፍል በሃላፊነት ተረጅነትን በማስወገድና እንደማህበረሰብ ከፍቺ፤ ከሱስ ከመሰል ቀውስን ሊያስከትሉ የበሚችሉ ነገሮች በአንክሮ በመመልከት ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በብዛት እየተስተዋለ ያለውን የሱስ ተጠቂነትን በመቀነስ ከስነ ልቦናና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ባሻገር ለጤና መቃወስ የሚዳርግ መሆኑንና የስራ ባህልን ከማዳከም ጀምሮ ስንፍናን የሚጭን ጎጂ ልማዶችን በማስወገድ ሀገራችንን የሚያስፈልጋት የጠንካራ ስራ ልምድ መቀየር እንደሚገባና ለዚህም ሁሉም ባለ ድርሻ አካል የበኩሉን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የእዣ ወረዳ ሰረተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ትዕግስት መንግስቱ በበኩላቸው ቤተሰብ የአንድን ማህበረሰብ ባህል፤ ወግና ስብዕና ለትውልድ በማስተማር የሚተጋ ተቋም መሆኑን ገልጸው የትኛውም ሰው በማህበረሰብ ውስጥ የሚያደርገው ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ከቤተሰቡ በሚወስደው ልምድ እንደመሆኑ ጥንቃቄያለው አስተዳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ጽህፈት ቤታቸውም መንግት ያወጣውን የማህበራዊ ደህንነት ልማት ፖሊሲ መመርያና ደንቦችን በማስፈጸም መፍትሄ የሚሹና የማህበራዊ ኑሮ ችግር ተጠቂ የሆኑትን ቤተሰቦችን አረጋዊያንን የአካል እና የአእምሮ ጉዳተኞችን ጨምሮ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመፍትሄ አቅጣጫ በመቀየስ ጥናት በማድረግ ማህበረሰቡን በማወያየትና ግንዛቤ በመፍጠር ድጋፍ እያደረገ እንዳለ እና ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

ቤተሰብ በግልጽ የመወያያትን ልማድ በማዳበር የመተጋገዝና መልካም ዕሴቶችን እንዲጠናከሩ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀው አጠቃላይ በማህበረሰቡ ዘንድ ሊፈጥሩ የሚችሉ የፍቺ የሱስ የደካማ የስራ-ባህልን እንዲሁም የህገወጥ ስደትን አስከፊነት በማስረዳት ግንዛቤ በመፍጠርና ተጋላጮችን በተለያዩ ጊዜ እና በተለያዩ ሁኔታዎች ጽ/ቤታቸው እያገዘና እየደገፈ መሆኑን አስረድተው ሁሉም ባለድርሻ አካላትም ለዚህ ተግባር እንዲተባበር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ስለ ማህበራዊ ቀውሶችና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠርና የሚከሰቱ የቀውስ አይነቶችን ጭምር በመጥቀስ እንዴት ሊፈቱ እንደሚችልና በቀጣይ ምን መስራት እንደሚገባ ሰፊ ውይይት ተደርጎ በመግባባት መድረኩ ተጠናቋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።

ምግብና ስርዓተ ምግብን በማሻሻል እና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ጤናማ ህፃናትንና ጤናማ እናትነትን ማረጋገጥ

ምግብና ስርዓተ ምግብን በማሻሻል እና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ጤናማ ህፃናትንና ጤናማ እናትነትን ማረጋገጥ በሀገርና በትውልድ ግንባታ ላይ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ።

ቀን 10/06/2018

‘’በምግብና ስርአተ-ምግብ፣ቤት ውስጥ ከመውለድ ነጻ ቀበሌዎች መፍጠርና “ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” Innovation and sustainable financing for safe motherhood,በሚል መሪ ቃል በእዣ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት አዘጋጅነት የንቅናቄ መድረክ ተካሄደ ።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ እንዳሉት በምግብና ስርዓተ-ምግብ ላይ የምናውለው መዋዕለ-ንዋይ በሀገርና በትውልድ ግንባታ ላይ የሚውል መዋዕለ-ንዋይ እንደሆነና ከምግብና ስርዓተ-ምግብ ጋር ተያይዞ የሚመጣው መቀጨጭና መቀንጨር መከላከል ስንችል ጤናማ፣በትምህርቱ ውጤታማ፣አምራች፣በስነ-ምግባሩ የታነጸና የፈጠራ ባለቤት የሆነ ትውልድ መፈጠር እንደሚገባ ገልዋል ።

ማህበረሰቡን ወደኋላ ሊመልስ የሚችሉን ነገሮችን በማጥናት ሳይንሳዊ ነገሮችን ከማህበረሰቡ የአኗኗር ስርዓት ጋር በማዋሀድና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ውስጥ በማስገባት ትርጉም ባለው መንገድ ለውጥ እንደሚገባና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እና በስራ ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።

የእናቶች ኮንፈረንስን በማጠናከር የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን በማስተካከል በአስተሳሰብ ክፍተት ምክንያት የእናትና ህፃናትን ሞት እንዳይፈጠርና ለእናቶችና ህፃናት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ሁሉም በየደረጃው ኃላፊነቱን ወስዶ መስራት እንደሚገባ አቶ ዘውዱ አሳስበዋል።

የእዣ ወረዳ ጤና ጽ/ ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ ሰኢድ በበኩላቸው በምግብና ስርዓተ-ምግብ ዙሪያ መሰራት ያለባቸው ስራዎች በአግባቡ ባለመከወናቸው የቀነጨረና የቀጨጨ ትውልድ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑንና ጥናቶች እንደሚያሳዩና እንደ ክልላችን በመቀንጨር 40%፣በመቀጨጭ 10 % በደምማነስ 15%፣ እንደዞናችን በተደረገው የዳሰሳ ጥናትም የመቀንጨር ጫና 28% ሲሆን የወረዳችንም ጫናው ከዚህ ያለፈ እንዳልሆነ ገልፀው፡፡

የዚህ ችግር መንስኤ ተደርጎ የሚወሰደው የስርአተ-ምግብ ልየታ (ከ5 አመት በታችና የእርጉዝና አጥቢ እናቶች) ልየታ ስራችን ውስንነት መሆኑን እና ልንቀይረው የሚገባ ነው ያሉት ኃላፊው የጤናማ እናትነት ቀን ስናከብር እናት ካረገዘችበት ቀን ጀምሮ የምንሰራቸው ስራዎች የመጨረሻ ግባችን ጤናማ እናትነት ማረጋገጥ ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል።

የእርጉዝ እናቶች ልየታ በጊዜና በጥራት መከወን ከ12 ሳምንታት በፊት የቅድመ ወሊድ ክትትል መጀመር.የቅድመ ወሊድ ክትትል 8ዙር ማድረስ እንዲሁም እናቶች ከወለዱ በኋላ በጤና ተቋም 24 ሰአት ማቆየትና በአጠቃላይ ቤት ውስጥ ከመውለድ ነጻ የሆኑ ቀበሌዎች መፍጠር ስንችል ጤናማ እናትነት ማረጋገጥ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።

በመድረኩም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነዶች የቀረቡ ሲሆን በሰነዱም ዙሪያ ሠፋ ያለ ውይይት በማድረግ እና በመግባባት እንዲሁም የቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ነው

በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ብልፅግና ፖርቲ የወጣቶች ክንፍ ፅ/ቤት

በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ብልፅግና ፖርቲ የወጣቶች ክንፍ ፅ/ቤት አዘጋጅነት በብልፅግና ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ፡አሠራሮችና መርሆዎች ላይ ለወጣቶች ክንፍ አባላት የተዘጋጀ የጥያቄና መልስ ውድድር መድረክ ተካሄደ።

የካቲት 10/2018 ዓሞ

በእለቱም የእዣ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ አዳነ ጄዛ እንዳሉት ኢትዮጵያን በተግባር ተምሳሌት ሀገር ለማድረግ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተናግረዋል።

ሀላፊው አክለውም ለትውልድ ተሻጋሪ ስራ ስናስብ ሁሌ በመደመር ዕሳቤ ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግና የተግባባ ማህበረሰብ ለመገንባት በጋራ መቆም ይገባል ።

የእዣ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ አብዶ ሁሴን በበኩላቸው ብልጽግና ፓርቲ የትውልድ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን በየደረጃው ያለው ወጣት ይህንን በመረዳት የሚመጥን የሀገር ግንባታ ስራ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ባለፉት አመታት በፓርቲና በመንግስት የተሰሩ ስራዎች ሲገመገሙ የወጣቱ ድርሻ ቀላል እንዳልነበረም የተናገሩት አቶ አብዶ በመሆኑም የህዝባችን ተጠቃሚነት ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።

የእዣ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ፅ/ቤት የወጣቶች ማብቃት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ታበዞ እንዳሉት ወጣቶች በየአደረጃጀታቸው ጠንካራና ሀገር አሻጋሪ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የተናበበ፡ የተግባባና አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር ግንባር ቀደም ሚና መጫወት አለባቸውም ብለዋል።

ቀጣይ ሚካሄደር 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ ፡ ፍትሀዊና ተአማኒነቱን ያለውና በመጨረሻም በህዝቡ ዘንድ ቅቡልነቱ የተረጋገጠ ምርጫ እንዲሆን ወጣቶች በግንባር ቀደምትነት መስራት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም በጥያቄና መልስ ውድድሩ ተሳትፈው ከ1እስከ 3 ለወጡ የወጣት ክንፍ አባላት እውቅናና ሽልማት በመስጠት መድረኩን ተጠናቋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።

የጉራጌ ዞን እግር ኳስ ቡድን

ዛሬ በተጀመረው ክልላዊ እስፖርታዊ ውድድሮች አስተናጋጁ የጉራጌ ዞን በእግር ኳስና በአትሌቲክስ ጫወታዎች ድል ቀንቶታል!!

የጉራጌ ዞን እግር ኳስ ቡድን የም ዞን 3 ለ0 በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።

3ኛው የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ልዩ ልዩ ሻምፒዮና፣ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል መጀመሩ ይታወቃል።

በመሆኑም የጉራጌ ዞን የእግር ኳስ ቡድን ከየም ዞን አቻው ጋር ባደረገው ብርቱ ፉክክር 3 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።

የጉራጌ ዞን፣ የም ዞን፣ ሀላባ ዞን እና ማረቆ ልዩ ወረዳ በመድብ አንድ ተደልድለዋል።

በአትሌቲክስ በሴቶች 1ሺ500 1ኛ ሲሆን

በወንድ 1ሺ 500 1ኛ እና 3ኛ በመዉጣት የወርቅ እና የነሀስ አሸናፊ ሆኗል።

የነፃ ህክምና ማስታወቂያ

የነፃ ህክምና ማስታወቂያ

ሰንራይዝ ዴቨሎፕመንት በተሰኘ ሀገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት አማካኝነት የተለያዩ ስፔሻሊስት ሀኪሞች ቡድን የነፃ ህክምና ለመስጠት ከየካቲት 12-15/ 2018 ዓ.ም አገና ጤና ጣቢያ ስለሚመጡ ከአንገት በላይ ( የጆሮ፣ የአይን እና የጥርስ) ህመም፣ የማህፀንና ተያያዥ ህመም፣ እና ሌሎችም የህፃናት እና የአዋቂዎች ህክምና ስለሚሰጥ ከላይ የተዘረዘሩትን እና ተያያዥ የጤና ችግር የገጠመው ማንኛውም ሰው አገልግሎቱን ማግኘት ስለሚችል በተጠቀሰው ቀን አገና ጤና ጣቢያ በመገኘት ተጠቃሚ መሆን ትችላላችሁ።