
===========================

===========================

=====================

=======================
እንሰት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ተቋቁሞ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዝ በመሆኑ በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል – ተመራማሪዎች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2016(ኢዜአ)፦ እንሰት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የመቋቋም ከፍተኛ አቅም ያለውና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዝ በመሆኑ በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የዘርፉ ተመራማሪዎች ገለጹ።
ዋና መቀመጫውን እንግሊዝ አገር ያደረገው ሮያል በተሰኘው የእጽዋት ምርምር ተቋም የዘርፉ ተመራማሪዎች፤ እንሰት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የመቋቋም አቅም እንዳለውና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ተናግረዋል።
በተቋሙ የእጽዋት ባህሪና ጥቅም ጥናት ቡድን መሪ ጀምስ ቦሬል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በግብርና ብዝኃ ሕይወትና አዝርት ስብጥር እምቅ አቅም ካላቸው አገሮች አንዷ መሆኗን ተናግረዋል።
የምርምር ተቋሙ ላለፉት 40 ዓመታት እንሰት ድርቅንና የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ያለውን ጥንካሬ በተመለከተ ጥልቅ ምርምር ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው ኢትዮጵያ በዓለም ልዩ የሆነው የእንሰት ምርት መገኛ መሆኗን ገልጸዋል።
እንሰት ወቅት ሳይጠብቅ በማንኛውም ጊዜ መመረት የሚችልና ለረዥም ጊዜ በማስቀመጥ ለምግብነት የመዋል ከፍተኛ አቅም እንዳለውም ጠቁመው በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ ሮያል የእጽዋት ምርምር ተቋም ላለፉት ስምንት ዓመታት የእንሰት መገኛን ለመለየት እንዲሁም ድርቅን የመቋቋም አቅሙን ለማወቅ ጥናት ሲያካሂድ ቆይቷል።
ይህንንም ተከትሎ በተለይም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን የተለያየ ዝርያ ያላቸውና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም ያላቸው የእንሰት እይነቶችን መለየታቸውን ተናግረዋል።
በሮያል የአጽዋት ምርምር ተቋም የብዝኃ ሕይወት ጥበቃና ትንተና ባለሙያ ሶፊ ሪቻርድስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተለያዩ የአዝርት እንዲሁም የእንሰት እይነቶች የታደለች መሆኗ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ 300 የአርሻ ቦታዎችን መጎብኘታቸውን ጠቅሰው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የግብርና ብዝኃ ህይወት ጥበቃ ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን እንደተገነዘቡ ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች ለእንሰት ምርት እያደረጉ ያለው ጥበቃና እንክብካቤ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ እስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
እንሰት በቀጣይ ከፍተኛ የምርት መጠን በመስጠትና ድርቅን ለረዥም ጊዜ በመቋቋም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚጣጣም የምርት አይነት እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
አርሶ አደሮች የእንሰት ዝርያን በመጠበቅና እንክብካቤ በማድረግ በርካታ ዝርያዎችን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
እንሰት ድርቅና የተለያዩ በሽታዎችን የመቋቋም ከፍተኛ አቅም ያለው ሲሆን በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ዋና ምግብ ሆኖ እንደሚያገለግል መረጃዎች ያመላክታሉ።

========================
መጋቢት 5/2016 ዓ/ም
የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ከጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ጋር በመተባበር የጉራጊኛ ቋንቋና ባህል ሊያሳድግ የሚያስችል አፕልኬሽን አስመረቀ።
የጉራጊኛ ቋንቋ በማልማትና በማሳደግ የስራና የሚዲያ ቋንቋ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጹ።
ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በምረቃ ፕሮግራሙ ተገኝተው እንዳሉት የጉራጌ ማህበረሰብ የራሱ ባህል፣ማንነት፣ወግ፣እሴት ያለው ሲሆን ያለው ቋንቋ ከማሳደግና ባህሉን በደንብ እንዲተዋወቅ ከማድረግ አንጻር ውስንነቶች የነበሩ ሲሆን ይህንን በቁጭት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የጉራጊኛ ቋንቋ ማሳደግ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ላጫ የአሰራርና የህግ ማዕቀፍ በመዘጋጀት፣በዞን ምክር ቤት እንዲፀድቅ በማድረግ የስራ ቋንቋ እንዲሆንና የጉራጊኛ ቋንቋ በ1ኛ ክፍል የተጀመሩው የመማር ማስተማር ስራ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ትምህርት እንዲሰጥበት ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆ ስራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል ።
የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እንዳሉት ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂ ዘመን ለመድረስ የጉራጊኛ ቋንቋ ለማሳደግ ጉራጊኛ፣አማሪኛና እንግሊዘኛ መዝገበ ቃላቶች የያዘ አፕልኬሽን ነው ዛሬ በይፋ መመረቁን የገለጹት።
ይህ የበለጸገው የጉራጊኛ አፕልኬሽን ጸሀፊዎች፣ተመራማሪዎች፣አጥኚዎችና ማንኛውም አካል መረጃን በቀላሉ እንዲያገኝ፣ቋንቋው እንዲያድግ እንዲሁም ስለ ጉራጌ ባህልና ቋንቋ ሙሉ እውቀት እንዲኖረው ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።
ጉራጌ ባህሉ፣ቋንቋው ታሪኩ እንዳያድግና እንዳይተዋወቅ የሚፈልጉ ከፋፋይ አካላት እንዳሉ ያስገነዘቡት ወ/ሮ መሰረት በቀጣይ ግን ቋንቋው እንደ ሌሎች ቋንቋዎች እንዲያድግ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት፣ተራዶ ድርጅቶችና ከሙህራን ጋር ተቀናጀተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ በበኩላቸው ሲስተሞችን በማልማትና በተቋማት ጥቅም ላይ ማዋል በዚህ ዘመን አማራጭ የሌለው የቴክኖሎጂ ትሩፋት ሲሆን እነዚህም ስራን ያቀላሉ፣ጊዜንና ወጪን ይቆጥባሉ ነው ያሉት።
አቶ ደምስ አክለውም ይህ አፕልኬሽን የጉራጊኛ ቋንቋና ባህል ከመጥፋትና ከብረዛ ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት በቴክኖሎጂ ለማገዝና በትምህርት ቤት የተጀመረው የጉራጊኛ ቋንቋ ተማሪዎች በትርጉም እንዳይቸገሩ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አብራርተዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ አካላት እንዳሉት የጉራጊኛ ቋንቋ እንዲያድግና የስራ ቋንቋ እንዲሆን በምክር ቤት ጸድቆ የህግ ማቀፍ እንዲኖረው መደረግ እንዳለበትና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል ።
ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው፣ጉራጊኛ የሚዲያ ቋንቋ መደረጉ እና መሰል አይነት በቴክኖሎጂ ተደግፎ እንዲያድግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እንዲጠናከሩ ያስታወቁት ሀሳብ ሰጪዎቹ የጉራጊኛ ቋንቋ ተናጋሪው ከራሱ ጀምሮ ጉራጊኛ በማውራት ቋንቋውን ማሳደግ እንዳለበት አስገንዘበዋል።
በመጨረሻም ለስራው ውጤታማነት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትና ተቋማት የእውቅና ሽልማት በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል ።

=====================

=================





*=======================================*







*========================*

=========================

=====================






©2023. የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት ከአገና ኮንስትራክሽን እና ኢደስትሪያል ኮሌጅ ጋር በመተባበር. All Rights Reserved.